ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዜጎች የጋራ ጥረት ውጤት እና የመንግስት የልማት ስኬት የሚገለጽበት አንዱ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዜጎች የጋራ ጥረት ውጤት እና የመንግስት የልማት ስኬት የሚገለጽበት አንዱ ማሳያ ነው
ባህር ዳር ፤ሰኔ 13/2017 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዜጎች የጋራ ጥረት ውጤትና የመንግስት የልማት ስኬት የሚገለጽበት አንዱ ማሳያ መሆኑን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሑሴን (ዶ/ር) ገለጹ።
በህዳሴ ግድብ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሑሴን (ዶ/ር)፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከኢትዮጵያ የልማት ስኬት ማሳያዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ የዜጎች የጋራ ጥረት ውጤትና የመንግስት የልማት ስኬት የሚገለጽበት ስለመሆኑም አንስተዋል።
ኢትዮጵያዊያን በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በሀሳባቸው ጭምር በህብረ ብሄራዊ አንድነት ግንባታውን ጀምረው ያገባደዱት የጋራ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እስከሚጠናቀቅ የዜጎች ሁለንተናዊ እገዛና ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት አንስተው የጋራ ልማትና አሰባሳቢ ትርክት የመገንባቱ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ከልማትና የሀገር ግንባታ አጀንዳ በተቃራኒ በመቆም በጫካ ትጥቅ አንስተው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የመንግስትን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በመቀበል ከጥፋት እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ድጋፍ አሰባሳቢና አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አባይነህ ጌጡ፤ ለግድቡ ግንባታ መሳካት የክልሉ ህዝብ ላደረገው የላቀ አስተዋጽኦ እና የነቃ ተሳትፎ አመስግነዋል።
የክልሉ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ከመጀመሪያው እስካሁን እገዛው መቀጠሉን ጠቅሰው በዚህ ዓመት ብቻ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
በቀጣይም በጋራ ልማትና አሰባሳቢ ትርክት ህብረ ብሄራዊ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።