ቀጥታ፡

ተስፋን ያለመለመው የብርሃን ስጦታ...

አዲስ አበባ፤ሰኔ 13/2017(ኢዜአ)፦ወጣት ፍሬው ሺበሺ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ተወልዶ ያደገ ሲሆን በለጋ እድሜው ነበር በድንገተኛ አደጋ ለአይን ብሌን ጠባሳ ችግር የተዳረገው።

በወቅቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረው ፍሬው ከትምህርቱ ጎን ለጎን የሞተር ሳይክል የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ራሱንም ቤተሰቡንም ያስተዳድር እንደነበር አስታውሷል።

ከአደጋው በኋላ አይኑ ላይ ያስተዋለው የህመም ስሜት እምብዛም በመሆኑ በወቅቱ ተገቢውን የህክምና ክትትል አለማድረጉንም ገልጿል።

ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ በአይኑ ላይ የተፈጠረውን አደጋ ተከትሎ የህመም ስሜቱ እየጨመረ ከመምጣቱ ባሻገር የእይታ መጠኑም እየቀነሰና የተባባሰ የጤና እክል አጋጥሞት መቆየቱን አብራርቷል። 


 

ይህ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ በሂደት ዐይኑ ሙሉ ለሙሉ ብርሃኑን ማጣቱን ይናገራል።

''በወጣትነት የአይን ብርሃንን ማጣት እጅግ አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ'' ነበር ሲል ሁኔታውን ገልጾታል።

በወቅቱ የገጠመው የተስፋ መቁረጥ ስሜትና ምንም አይነት ህክምና ለመውሰድ አለመፈለጉ ለስነ-ልቦና ጫና ዳርጎት እንደነበርም አይዘነጋውም። 

ከዓመታት በኋላ በቤተሰብ ጉትጎታ በዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአይን ህክምናውን ለመከታተል አዲስ አበባ ደርሷል።

በሆስፒታሉ አጠቃላይ የዐይን ምርመራ እንዳገኘ የገለጸው ወጣት ፍሬው በወቅቱ ስለ ዐይን ብሌን ቀዶ ህክምና ምንም ግንዛቤ እንዳልነበረው አስታውሷል።

የህክምና አገልግሎቱን በሚመለከት በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማስቻል የዐይን ህክምናውን መከታተል መጀመሩን ተናግሯል።

በተደረገለት ተከታታይ ህክምና የዓይን ብሌን ካገኘ ብርሃኑ እንደሚመለስ ተነግሮት ህክምናውን ያለማቋረጥ መከታተል እንደጀመረ ገልጿል። 

ይሁን እንጂ የዐይን ብሌን ማግኘቱ ቀላል እንዳልነበር አስታውሶ ከረጅም ግዜ ጥበቃ በኋላ ለሱ የሚሆን የዐይን ብሌን እንደተገኘለት ጠቁሟል።

የህክምና ባለሙያዎች በወቅቱ አስፈላጊውን የህክምና እርዳታ እንዳደረጉለት ገልጾ የዐይን ብሌን ቀዶ ህክምናው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ''የህይወቴ አዲስ ምዕራፍ ጅማሬ ነው'' ሲል ገልጿል።

ከህክምናው በኋላ ዐይኑ ሙሉ ለሙሉ ብርሃን እንዳገኘና ቀንና ጨለማን በአዲስ መልክ መለየት መቻሉ እጅግ እንዳስደሰተው ነው የሚናገረው።

የዐይን ብሌን ቀዶ ህክምናው ህይወቱ ካቆመበት እንዲቀጥል ትልቅ ተስፋ እንደሆነው ተናግሯል፡፡

የኔ ህይወት ለብዙዎች ተስፋ የሚሰጥ ነው ያለው ወጣት ፍሬው ሰዎች ከህልፈት በኋላ የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ከወዲሁ ቃል እንዲገቡና ብርሃንን ላጡ ብርሃን እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንከ አገልግሎት በበኩሉ በኢትዮጵያ የዐይን ብሌን ልገሳ ባህል እንዲሆንና እንዲዳብር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል። 


 

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች በተለያየ ምክንያት የአይን ብሌናቸውን እንዳጡ ጥናቶችን ጠቅሰው አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና ከሚሰጡ ውስን የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ማዕከል መሆኗን አብራርተዋል።

በመሆኑም ህክምናውን መጀመር ለሚፈልጉ የአፍሪካ አገራት ልምድና ተሞክሮን በማጋራት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተች ስለመሆኑም አንስተዋል።

ከተፈጥሮ ውጪ የሚያጋጥም የዐይን ብርሃንን የማጣት መንስኤ በዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና የመዳን እድሉ ሰፊ መሆኑን ገልጸዋል።

የዐይን ብሌን ከህልፈት በኋላ የሚለገስ ሲሆን የአይን ሙሉ ክፍሉን ሳይሆን በሳይንሳዊ ህክምና ዘዴ ብሌኗን ብቻ በጥንቃቄ የማንሳት ስራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የየትኛውም ሰው የዐይን ብሌን ለሁሉም ሰው እንደሚሆን ጠቁመው ከአንድ ሰው የተነሳ የዐይን ብሌን ለሁለት ሰዎች የዐይን ብርሃን መስጠት እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በመሆኑም የሚለገስ የዐይን ብሌን የዐይን ብርሃናቸውን ላጡ ሰዎች ፍቱን መፍትሄ በመሆኑ ዜጎች ከህልፈት በኋላ የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ከወዲሁ ቃል እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም