ቀጥታ፡

በሀገራዊ እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እንሰራለን-- የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2017(ኢዜአ)፦ፖለቲካዊ አመለካከቶች እንዳሉ ሆነው በሀገራዊ እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እንደሚሰሩ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ገልጸዋል።


 

ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ አባላት በኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘውን የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ጎብኝተዋል።

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የጠቆሙት የፖለቲካ ፖርቲ አባላቱ ፕሮጀክቱ እጅግ ግዙፍ እና ዘመን ተሻጋሪ የሀገር ሀብት ሆኖ እንዳገኙት ገልፀዋል። 

የግንባታ ሁኔታው ትልቅ ምሳሌ እንደሆነ እና የግንባታው ደረጃም ከገመቱት በላይ ሆኖ እንዳገኙት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ፕሮጀክቱ የተባበሩ ክንዶች ውጤት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ያለውን ሀብት በመለየት በዚህ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለ ሀገር በአጭር ጊዜ መለወጥ ትችላለች ብለዋል ።


 

በሀገሪቱ እየተከናወኑ በሚገኙ ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ በኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን ግንባታው ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ሲገባ 1800 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም አለው።


 

ይህም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ከፍተኛ ኃይል አመንጪ ግድብ ያደርገዋል።

‎በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው ፕሮጀክቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በኮንታ ዞን ኮንታ ኮይሻ ወረዳ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ መካከል ላይ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ የሁለት ክልል ህዝቦችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በሚፈታ መልኩ እየተገነባ እንደሚገኝም የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ተናግረዋል።


 

የአካባቢው ተፈጥሮ ይበልጥ ተጠብቆ የሚለማበትና ለቱሪስት መስህብ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ 65 በመቶ መድረሱን የገለጹት አስተባባሪዎች፥ ፕሮጀክቱን ‎ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

‎

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም