ኢትዮጵያን ለመገንባት ፉክክር ብቻ በቂ አይደለም ትብብር ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ለመገንባት ፉክክር ብቻ በቂ አይደለም ትብብር ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ የፖለቲካ ምህዳሩ ለውጥ አካል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው ጠንክረው እና ሀሳብ ኖሯቸው ከመጡ ከሚፎካከሩን ጋር በትብብር ለመስራት በራችን ክፍተ ነው ብለዋል።

ለዚህ ዋናው መስፈርቱ ግን ኢትዮጵያ አንድ ታላቅ ሀገር ሆና እንድትቀጥል በመንግስትም ሆነ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል በተሰወነ ደረጃ የመተው ልምምድ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በካቢኔ አባልነት አብረውን እየሰሩ ያሉ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ማክሮ ኢኮኖሚን ጨምሮ በበርካታ አጀንዳዎች ላይ በመከራከርም በመቃረንም ሆነ በመጠየቅ አብረን ስንሰራ አራት ዓመታት ሆነውናል ብለዋል።

እንዲህ አይነት የትብብር ልምምድ ካላካበትን በጋራ ሀገር ልንሰራ ስለማንችል ይህም ከውጊያው እና ከስደቱ ስለሚሻል ነው አብረን እየሰራን ያለነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ለዚህ ነው ፉክክር ብቻ በቂ አይደለም ትብብር ያስፈልጋል የምንለው ባንግባባ እንኳን እየተባበርን ኢትዮጵያን ብንገነባ ይሻላል የሚል ሀሳብ አለን ሲሉም አክለዋል።

ይህንንም ተናግረናል ጽፈናል ደግሞም ልንኖረው እየሞከርን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህም ሙሉ ካልሆነ እናሰፋዋለን ብለዋል።

ነገር ግን ከዲሞክራሲ ልምምድ ችግር የተነሳ በየቦታው ውስንነቶች እንደሚኖሩ ጠቁመው ለውጡን እያየን የጎደለውን እየሞላን ብንሄድ የተሻለ ሀገር ለመፍጠር ያግዛል ነው ያሉት።

ቀደም ሲል በነበረን ውይይት በዞን እና በወረዳ ደረጃ ችግር እየገጠማችሁ እንደሆነ ባነሳችሁት መሰረት ከሁሉም ክልሎች ጋር በመነጋገር ሁሉም ዞኖች እንዲያነጋግሯችሁ ተደርጎ ከሰላሳ በላይ ጉዳዮች መቀረፋቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም እስከ ዞን ድረስ ባለው መዋቅር የሚገጥሟችሁን ችግሮች ለመፍታት ምርጫ ቦርድ የመንግስትን ተሳትፎ ሲጠይቅ ከፍተኛ የስራ ሀላፈዎችን እየመደበ እንዲጣራ እያደረገ ያለው ጉዳዩ እንዳይታፈን ስለምንፈልግ ጭምር ነውም ሲሉም ተናግረዋል።

በጎደለው ደግሞ እንዲህ ስንገናኝ ግብዓት እየወሰድን እያረምን ለመሄድ ነው ያለው ፍላጎት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደፓርቲ ውስጣችንንም በየጊዜው እየገመገምን እያረምን የምንሄደው ለዚሁ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም