ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኮከቦች ሽልማት ሰኔ 19 ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2017 (ኢዜአ)፦  የ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኮከቦች ሽልማት ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።

የሽልማት ስነ ስርዓቱ ሰኔ 19 በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ስሑል ሽሬ እና ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ መድን ከሚያደርጉት የሊጉ የመዝጊያ ጨዋታ በኋላ በልዩ ሁኔታ እንደሚከናወን ገልጿል።

በዕለቱ የዓመቱ ምርጦች ይሸለማሉ ያለው አክሲዮን ማህበሩ የአሸናፊው የዋንጫ ፕሮግራም እንደሚከናወንና ሙሉ ፕሮግራሙ በሱፐር ስፖርት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝ አመልክቷል።

በተያያዘም ማህበሩ ሽልማት የሚሰጥባቸውን ዘርፎች ይፋ አድርጓል። 

የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች፣ የዓመቱ ኮከብ ተስፈኛ ተጫዋች፣ የዓመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ፣ የዓመቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ፣ የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ፣ የዓመቱ ምስጉን ዋና ዳኛ እና የዓመቱ ምስጉን ረዳት ዳኛ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የ2017 የሊጉን ኮከብ ተጫዋች እጩዎች ዝርዝር ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት ከሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ መድን ሀይደር ሸረፋ፣ መሐመድ አበራ እና ዳዊት ተፈራ ፣ ራምኬል ጀምስ እና ዲቫይን ዋቹኩዋ ከኢትዮጵያ ቡና፣ የሃዋሳ ከተማው ዓሊ ሱሌይማን እና የመቻሉ ሽመልስ በቀለ በእጩነት ቀርበዋል።

በኮከብ ወጣት ተስፈኛ ተጨዋች ዘርፍ በረከት ካሌብ ከኢትዮጵያ መድን፣ ይታገሱ ታሪኩ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ሄኖክ ዮሐንስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሄኖክ ይበልጣል ከባህር ዳር ከተማ እና ዘረሰናይ ብርሃነ ከመቀሌ 70 እንደርታ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትዋል።

አቡበከር ኑራ ከኢትዮጵያ መድን፣ ዳንላንድ ኢብራሂም ከኢትዮጵያ ቡና እና ፔፔ ሰዒዶ ከባህር ዳር ከተማ የኮከብ ግብ ጠባቂ እጩዎች ናቸው። 

ተመልካቾች በተለያየ ዘርፍ የቀረቡትን ተጫዋቾች ከሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ https://t.me/ethiopianlea የአክሲዮን ማህበሩ የቴሌግራም ገጽ ድምጽ እየሰጡ ይገኛል። 

የድምጽ አሰጣጡ እስከ ዛሬ ከንጋቱ 12 ሰዓት በፊት ይጠናቀቃል።    

ከተመልካቾች ድምጽ በተጨማሪ አሰልጣኞች፣ ጋዜጠኞችና የሊጉን ጨዋታ የቀጥታ ስርጭት መብት የወሰደው የደቡብ አፍሪካው ሱፐር ስፖርት የቴሌቪዥን ጣቢያ በድምጽ አሰጣጡ ድርሻ እንዳላቸው ማህበሩ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም