የገጠር ኮሪደር ልማት ለአካባቢ ጽዳትና ለምርታማነት ማደግ የጎላ አበርክቶ አለው

ሆሳዕና፤ ሰኔ 13/2017 (ኢዜአ)፡- የገጠር ኮሪደር ልማት ፅዱ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት የጎላ አበርክቶ እንዳለው ተመላከተ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት የገጠር ኮሪደር ልማት አገርን የመለወጥ ሰፊ ራዕይ የተሰነቀበት አገራዊ ውጥን መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።

ይህንንም መሰረት በማድረግ በገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች እያንዳንዱ አርሶ አደር ከነበረው የተሻለ የአኗኗር ዘይቤን እንዲከተል በማድረግ የተለየ ስልተ ምርት ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ህይወቱ እንዲለወጥ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።


 

ይኸው ተግባርም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈም ለስራ ዕድል ፈጠራ አበርክቶው እየጎላ መምጣቱም ተገልጿል። 

በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ  ለማሳደግ የገጠሩን ማህበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻል ላይ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

ይህም ገጠሩን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ለምርትና ምርታማነት ማደግ ካለው አበርክቶ በተጨማሪ ለስራ እድል ፈጠራ ማገልገሉን ተናግረዋል፡፡ 

የገጠር ኮሪደር ልማት ፅዱና ውብ አካባቢን በመፍጠር የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ መቀየሩንም  ጠቅሰዋል።


 

በስልጤ ዞን አሊቾ ውሪሮ ወረዳ ስሎ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ዘምዘም ኑርገባ፤ በአካባቢያቸው እየተተገበረ የሚገኘው የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ ለኑሮ የተመቸ ንፁህ አካባቢን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተስተካከለ መንገድ  አለመኖር  ለማህበራዊና  ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጠው እንዲቆዩ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡


 

የዚሁ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ዋበላ ሀምዛ በበኩላቸው በአካባቢው በዓመት ሶስት ጊዜና ከዚያ በላይ   በማምረት ምርትና ምርታማነት ቢያድግም በመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነት ችግር ሳቢያ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

ይህን ችግር ለመፍታትም የገጠር ኮሪደር ልማቱ  የምርጥ ዘር አቅርቦትንና  ምርታቸውን ለማጓጓዝ  እንዳገዛቸው  ተናግረዋል፡፡

የገጠር ኮሪደር ልማቱ  ጽዱ  አካባቢን  በመፍጠርም  ጤናቸው እንዲጠበቅ ማገዙንም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም