ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል ለምታደርገው ድጋፍ ኔዘርላንድስ ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል ለምታደርገው ድጋፍ ኔዘርላንድስ ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል ለምታደርገው ድጋፍ ኔዘርላንድስ ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ ቀጣናዊ የስደተኞች ጉዳይ አስተባባሪ ታይስቲ ሶንዳል ገለጹ።
አስተባባሪው ታይስቲ ሶንዳል ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ እየተወጣች ያለውን ሚና አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ለስደተኞች ጥበቃ በማድረግ፣ የመስሪያ ፈቃድ በመስጠት፣ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑና የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን በአካታችነት የሚያስተናግድበትን አሰራር የኔዘርላንድስ መንግስት እንደሚደግፍ ነው አስተባባሪው የተናገሩት።
ኔዘርላንድስ የሰብዓዊና ልማት ድጋፍ በማድረግ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም እገዛው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ሀገሪቱ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ጨምሮ በስምንት ሀገሮች ላይ የሚተገበር የአራት ዓመት የልማት መርሃ ግብር እንዳላትም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በልማት ትብብር፣ በሰብዓዊ ድጋፍ እና ሌሎች ዘርፎች ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ኔዘርላንድስ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ በንቃት ከሚሳተፉ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መካከል አንደኛዋ መሆኗን ጠቁመው፥ ሀገራቱ በግብርና፣ በውሃ አስተዳደር፣ በጤና አጠባበቅና በሌሎች ዘርፎችም ጠንካራ ትብብር አላቸው ብለዋል።
በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጨምረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በአህጉሪቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኗን አመልክተው፤ ኔዘርላንድስ ከሀገሪቱ ጋር ያላትን ግንኙነት አስፈላጊነት በአጽንኦት አንስተዋል።