ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በማጽናትና በማልማት ላይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2017(ኢዜአ)፦ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባልተግባባንባቸው ጉዳዮች ላይ ብንከራከርም ኢትዮጵያን በማጽናትና በማልማት ላይ ግን አብሮ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሻለ ዲሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ እና አካታች ምርጫ እንዲካሄድ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር እንደሚያስፈልግም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተናገሩት፡፡


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእኛ እምነት ምርጫው አካታች እንዲሆን እንሰራለን፣ እናንተም ሰብሰብ እና ጠንከር በሉ መደገፍ ባለብን ነገር እናግዛለን ብለዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ህልሞች ስላሉት የሚወዳደረው ለማሸነፍ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖም ብልፅግና ብቻውን የሚይዘው ፓርላማ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለን አናስብም ነው ያሉት፡፡

እኛ ማሸነፍ እንደምንፈልገው ሁሉ የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ቢሳተፉ ይጠቅማል፣ ለዚህም ድጋፍ እንደሚደረግና የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በምርጫው የምንከራከርባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሁሉ በምንስማማባቸው ላይ አብረን ብንሰራ ፓርላማውም ሆነ መንግስት አካታች ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ እኛ ዝግጁ ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባልተግባባንባቸው ጉዳዮች ላይ ብንከራከርም ኢትዮጵያን በማጽናትና በማልማት ላይ ግን አብሮ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።


 

ካለፈው ምርጫ የተሻለ አካታችና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚካሄድ ጠቁመው ይህን የማይፈልጉ ሰዎች ቢኖሩም እኛ ኮሪደር እናለማለን፣ የስንዴ ልማትን እናስፋፋለን፣ ህዳሴን እናስመርቃለን፣ ምርጫ እናካሂዳለን ኢትዮጵያም ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

በየዞኑ የሚገጥሟችሁን ችግሮች በተመለከተ ከክልል አመራሮች ጋር ተነጋግረን ለመፍታት እንሰራለን የጎደለ ነገር ካለም እየተወያየን እንፈታለን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው።

የኢትዮጵያ ህልውና እና ሉዓላዊነት ስጋት የሆነበት ዘመን አልፏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አሁን ላይ ማንም ኢትዮጵያን በሀይል ማንበርከክ አይችልም፤ ኢትዮጵያ አንድ ናት አንድ ሆና ትቀጥላለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም