በኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ስራዎችን የሚያበረታቱ መደላድሎች ተመቻችተዋል- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

ወልቂጤ፤ ሰኔ 12/2017 (ኢዜአ) ፡-  በኢትዮጵያ በውጤታማነት የቀጠሉ  የልማት ተግባራትን የሚደግፉና  ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂና  ፈጠራ ስራዎችን የሚያበረታቱ መደላድሎች  መመቻቸታቸውን  የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

"ክልሉን የሳይንስ ማዕከል እናድርግ" በሚል መሪ ሀሳብ  በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሁለተኛው ዙር የሳይንስና ፈጠራ አውደ ርዕይ እና ውድድር  በወልቂጤ ከተማ  እየተካሄደ ነው።


 

ለሁለት ቀናት የሚቆየውን ይህንን መረሃ ግብር ያዘጋጁት የክልሉ ትምህርት፣ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የስራ እድል ፈጠራና ኢንተንርፕራይዝ ቢሮ በጋራ እንደሆነ ተመልክቷል።

በመክፈቻው መረሃ ግብር ላይ ከተገኙት መካከል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር)፤ ባደረጉት ንግግር፤ የሃገሪቱን ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተያዙ የልማት ግቦችን መደገፍ የሚያስችሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

ዘመኑን የዋጁ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ልማቱን ዘላቂና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያጠናክሩ በመሆናቸው በዘርፉ የተሰማሩትን የሚያበረታታና የሚያጎለብት መደላደል መመቻቸቱን ገልጸዋል።


 

በዚህም ጊዜው የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ውጤት የሚያመላክቱ ፈጠራዎችና ቴክኖሎጂዎች እየታዩ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

የቴክኖሎጂና ፈጠራ ስራዎችን ሀገራዊ የልማት ግቦች ከመደገፍ አልፎ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ እና ተወዳዳሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች  የሚያበረታታ አሰራር ተዘርግቷል ሲሉም አንስተዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ ገበያ መር የኢኖቬሽን ፣ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ  እድገት የሚያበረታታ አሰራር በአዲሱ የትምህርት ስልጠናና ስርዓት መካተቱን ገልጸዋል ።


 

አዳዲስ ሃሳብ በማፍለቅ ጊዜ ጉልበትና ገንዘብ የሚቆጥቡ ፈጠራ ላይ ተማሪዎችን በማሳተፍ እየተሰራ እንደሆነም አንስተዋል። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር፣የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አንተነህ ፍቃዱ፤ ቴክኖሎጂ  ማህበራዊ ልማትን  ለማረጋገጥ ያለው ድርሻ የላቀ ነው ብለዋል።


 

በዚህም በክልሉ ሁሉን አቀፍ ልማት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ በየአካባቢው በፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩትን የማበረታታት ተግባር እየተከናወነ  መሆኑን ገልጸዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፈጠራ ስራን ለማጠናከር ለሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ያሉት ደግሞ የክልሉ ሳይንስ ፣ኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሀላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ናቸው  ።

ምርምር እና ፈጠራን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድም በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። 


 

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ፤ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በዞኑ ተወዳዳሪና ስኬታማ ዜጎች ማየት መቻሉን አንሰተው፤ በተማሪዎችና መምህራን የተከናወኑ  ስራዎች  አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው መደረጉ ብዙዎች ወደዚህ እንዲሳቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን  ገልጸዋል። 


 

በመረሃ ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና አፈጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎን ጨምሮ  ሌሎችም አመራሮችና ባለድርሻ አካላት  እየተሳተፉ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም