በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2017 (ኢዜአ)፦ በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ የምድብ አንድ እና ሁለት ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።
በምድብ አንድ ፖልሜራስ ከአል አህሊ ምሽት 1 ሰዓት ላይ በሜትላይፍ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ፖልሜራስ በመጀመሪያ ጨዋታው ከፖርቶ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።
ተጋጣሚው አል አህሊ በዓለም ዋንጫው የመክፈቻ ጨዋታ ከኢንተር ሚያሚ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ መውጣቱ የሚታወስ ነው።
በዚሁ ምድብ ኢንተር ሚያሚ ከፖርቶ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ በሜርሴዲስ-ቤንዝ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በምድቡ የሚገኙ ክለቦች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ለማሸነፍ ይጫወታሉ።
በምድብ ሁለት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ፒኤስጂ ከቦታፎጎ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በሮዝ ቦውል ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ፒኤስጂ በመጀመሪያ ጨዋታው አትሌቲኮ ማድሪድን 4 ለ ዐ ሲረታ፤ ቦታፎጎ ሲያትል ሳውንደርስን 2 ለ 1 አሸንፏል።
የጨዋታው አሸናፊ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቱን ያረጋግጣል።
በዚሁ ምድብ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን የተሸነፉት ሲያትል ሳውንደርስ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ በሉመን ፊልድ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ጨዋታው ክለቦቹ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ፍልሚያ ነው።
ተሸናፊው ክለብ ከውድድሩ የሚሰናበት የመጀመሪያ ቡድን ይሆናል።
በአሜሪካ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል።