በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ስራን ባህል ማድረግ የህልውና ጉዳይ ሊሆን ይገባል- ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ስራን ባህል ማድረግ የህልውና ጉዳይ ሊሆን ይገባል- ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 12/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ስራን ባህል ማድረግ የህልውና ጉዳይ ሊሆን ይገባል ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
"የስራ ባህልና ምርታማነት ለሀገር ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
የፓናል ውይይቱ በስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
በመድረኩም የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር)፣ የስራ ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፣ የፌዴራል እና ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የፓናል ውይይቱ የስራ ባህልን በማሻሻል፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ ከህሎትን በማልማት አገራዊ ዕድገትን ዕውን ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ጠንካራ የስራ ባህልን ማጎልበት ይገባል።
በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ስራን ባህል ማድረግ የህልውና ጉዳይ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በዚህም በአካባቢው ያለውን ጸጋ ተጠቅሞ ሰርቶ ለማደግ ከቤተሰብ ጀምሮ ያለው የስራ ባህል እንዲለወጥ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
የስራ ባህልን ለመገንባት የተያዘው ግብ የሚሳካው የማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ሲያድግ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ሚኒስቴሩ ምክክር እያካሄደ ነው ብለዋል።
የምክክር መድረኩ የቤተሰብ ማህበረሰብ ምርታማነት ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵ የዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የስራ ባህል እንዲገነባ የልምድ ልውውጥ እና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ቀጣይነት ባለው መልኩ ማካሄድ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
አገራዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የስራ ባህል ለመገንባት የባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ የዛሬው መድረክም ይሄው ግብ እንዲሳካ ትልቅ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
ኢዜአ ከዜና እና ዜና ነክ ባሻገር አገራዊ መግባባት ጉዳዮች ላይ አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።