በክልሉ ፈጥኖ ለሚደርስ የቡና እና የፍራፍሬ ችግኝ መትከያ የሚውል ከ13ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ፈጥኖ ለሚደርስ የቡና እና የፍራፍሬ ችግኝ መትከያ የሚውል ከ13ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተዘጋጀ

ባህርዳር፤ ሰኔ 12/2017 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ፈጥኖ የሚደርስ እና የተሻለ ምርት የሚሰጥ የቡና እና የፍራፍሬ ችግኝ መትከያ ከ13ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር በክልሉ ከተተከለው የቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኝ ውስጥ 92 በመቶ መፅደቁም ተገልጿል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ግርማ በቀለ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ፈጥኖ የሚደርስና የተሻለ ምርት የሚሰጥ ከ17 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኝ ለተከላ ተሰናድቷል።
ቡና ነባሩ ዝርያ ለምርት ለመድረስ እስከ ሰባት ዓመት የሚፈጅበት በተሻሻለው ዝርያ ወደ ሶሰት ዓመት ዝቅ ብሎ መድረስ እንደሚቻል በምርምር መረጋገጡን አስረድተዋል።
በምርት ረገድም ነባሩ የቡና ዝርያ በሄክታር ሶስት ኩንታል የሚሰጠውን በተሻሻለው ወደ ስድስት ነጥብ አምስት ኩንታል ለማሳደግ እንደሚያስችል አመላክተዋል።
ከፍራፍሬ ውስጥም አቡካዶ የተሻሻለው ዝርያ በሄክታር እስከ 200 ኩንታል የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህም ከነባሩ ዝርያ ከእጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
ከተዘጋጀው አጠቃላይ ችግኝ ውስጥ ከ9 ሚሊዮን የሚበልጠው የቡና ሲሆን ቀሪው የአቡካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካን፣ ዘይቱን ፣አፕል እና ኮክ መሆኑን አስረድተዋል።
አብዛኞቹ ችግኞች ለቡና እና ለቆላ ፍራፍሬ ተስማሚ በሆኑ 36 ኩታ ገጠም ወረዳዎች እንደሚተከል አመልክተዋል።
ለቡናና ፍራፍሬ ችግኝ ተከላም ከ13ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
አርሶ አደር ሞላ ዘገዬ በምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢጠህናን ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ፤ የተሻሻለ የቡና እና አቦካዶ ችግኝ የግብርና ልማት መስሪያ ቤት ካዘጋጀው ችግኝ ጣቢያ ወስደው በሩብ ሄክታር መሬት ለመትከል መሰናዳታቸውን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በሩብ ሄክታር መሬታቸው ላይ የተከሉት የቡና ችግኝ ምርት መስጠት መጀመሩን አውስተዋል።
በአዊ ዞን የጓንጓ ወረዳ አርሶ አደር አድማስ አለነ በበኩላቸው፤ የቡና እና የፍራፍሬ ምርት በገበያ ላይ አዋጭ በመሆኑ በዘርፉ ልማት እየተሳተፉ ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከልማቱ የሚያገኙት ምርት ከፍጆታቸው አልፎ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
በክረምት ወቅትም ፈጥኖ የሚደርስና የተሻለ ምርት የሚሰጥ የቡና ችግኝ ለመትከል ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ከ150 በላይ የአቡካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝና የቡና ችግኝ ለመትከል ጉድጓድ እያዘጋጁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባህርዳር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር አለኸኝ መልኬ ናቸው።
ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ከተተከለው ከ14 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኝ ውስጥ 92 በመቶ ማፅደቅ ተችሏል።