ቀጥታ፡

በአጀንዳ 2063 ትግበራ በነባራዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የክትትልና ምዘና ስርአት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2017 (ኢዜአ)፦ በአጀንዳ 2063 ትግበራ አገራት በነባራዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ የክትትልና ምዘና ስርአታቸውን የበለጠ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ባለሙያዎች አመላከቱ።

በአፍሪካ የምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ ሽግግር ለማምጣት አላማ አድርጎ በአህጉሪቱ እየተተገበረ የሚገኘው አጀንዳ 2063 አካታችና ዘላቂ ልማት ማምጣት ዋነኛ ትኩረቱ ነው።

የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ በትምህርት የላቀ ማህበረሰብ መፍጠር፣ ምጣኔ ሃብትን ማሸጋገር እንዲሁም ሰላሟና አንድነቷ የተረጋገጠ አፍሪካን መፍጠር አጀንዳው ትኩረት ከሚያደርግባቸው መካከል ናቸው።

በአፍሪካ ጠንካራ የክትትልና ግምገማ ስርአት ለመዘርጋት የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የግምገማ ማህበር 25ኛ አመት የምስረታ በዓል ላይ የተሳተፉ ሙያተኞች ለኢዜአ ተናግረዋል።

በታንዛኒያ ዳሬሰላም ዩኒቨርስቲ የአፕላይድ ኢቲክስና ዲቨሎፕመንት ኢቫሊዮሽን መምህር አልማስ ፎርቱናተስ(ዶ/ር) አጀንዳ 2063 ለአፍሪካ ልማትና ብልጽግና አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በትግበራ ሂደት የአፍሪካን ህዝብ ፍላጎትና ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ የግምገማና ክትትል ስርአት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።


 

በካሜሮን "ውጤታማ መሰረታዊ አገልግሎት" በተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት የምዘና ባለሙያ ወጣት ኦክዌን ቻኒሴ በበኩሏ በአጀንዳ 2063 ወጣቱን እና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ምዘናን ማከናወን ወሳኝ መሆኑን አንስታለች።

ለዚህም ወጣት የምዘና እና ክትትል ባለሙያዎችን በማሳተፍ በተጨባጭ ክፍተቶችን እንዲያሳዩ እድል መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁማለች።

የኢትዮጵያ የግምገማ ማህበር ፕሬዝዳንት ደረጀ ማሞ አፍሪካ በለጋሽ ድርጅቶች ላይ ከተመሰረተ የግምገማ ስርአት በመውጣት የራሷን አሰራር በመዘርጋት ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ምዘና ስርአትን ተቋማዊ በማድረግ እየሰራች መሆኑን በማሳያነት አንስተዋል።


 

ለዚህም አጋዥ ይሆን ዘንድ የኢቫሊዮሽን ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ጠቅሰው የሰው ሃይል ለማብቃት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጀመረውን ስራ የበለጠ የሚያጠናክር ነው።

የኢትዮጵያ የግምገማ ማህበር የአገር በቀል ምጣኔ ሃብት መርሃ ግብርንና አጀንዳ 2063ን ግምት ውስጥ በማስገባት በብሔራዊና አህጉር ደረጃ የበኩሉን ለመወጣት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የምዘና ስርአት ተግባራዊ የሚደረጉ የልማት መርሃ ግብሮችን ለማሻሻል፣ ተጠያቂነትን ለማስፈንና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም