ቀጥታ፡

በዩኒዶ ሲተገበር የቆየው የቆዳ ምርት ጥራት ማስጠበቂያ ፕሮጀክት በዘርፉ ጥሩ መሰረት ጥሏል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2017(ኢዜአ)፦በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ሲተገበር የቆየው የቆዳ ምርት ጥራት ማስጠበቂያ ፕሮጀክት በዘርፉ ጥሩ መሰረት መጣሉን የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ (ዶ/ር) ገለፁ።

ላለፉት ሰባት ዓመታት በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ ሲተገበር የቆየው የቆዳ ዘርፍ ቀጣይነት ላለው የስራ ዕድል ፈጠራ (LISEC) ፕሮጀክት የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ተካሂዷል። 


 

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ ለወጣቶችና ለሴቶች ስልጠና በመስጠት ቀጣይነት ያለው የስራ እድል ፈጠራ ከሚሰጠው ፕሮጀክት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

ዩኒዶ ሊሳክ ፕሮጀክት በዋናነት የቆዳ ጥሬ ዕቃ ጥራት ማስጠበቅ ላይ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮችን ማቃለል ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል። 

ላለፉት ሰባት ዓመታት በዩኒዶ ሲተገበር የቆየው የቆዳ ምርት ጥራት ማስጠበቂያ ፕሮጀክት በዘርፉ ጥሩ መሰረት ጥሏል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ሞጆ በቀጣይ የሀገሪቱ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን መሠረት መጣል የሚችል የላብራቶሪ ማዕከል እንዲቋቋም፣ ዘርፉን ለማሳደግ ከተቋማት በቅንጅት በመስራት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነውም ብለዋል።  

በዚህም በሞጆ እና አካባቢዋ የሚገኙ የቆዳ ፋብሪካ ባለቤቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ የምስክር ወረቀት ባለቤት እንዲሆኑ እያደረጋቸው መሆኑንም ጠቁመዋል። 


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ልማት ዘርፍ የፕሮግራም ማናጀር አውሬሊያ ፓትሪዚያ ካላብሪዮ በበኩላቸው የቆዳ ጥሬ ዕቃ ጥራት ሊጠበቅ የሚችለው ከዕርድ ጀምሮ ያለው ሂደት በጥንቃቄ ሲከወን መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም እንዲረዳ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በሞጆ እና በአዲስ አበባ ከተሞች ስድስት ዘመናዊ የማረጃ ማሽኖችን ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።

ዘመናዊ ማሽኖቹ በዕርድ ወቅት የሚከሰትን የቆዳ ብልሽት ለመከላከል ዓይነተኛ ሚና በመጫወት ደህንነቱ የተጠበቀ የቆዳ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከኢንደስትሪ እና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በዘርፉ የሚታየውን ችግር በቀጣይነት ለማቃለል መሰረታዊ የሆኑ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እና ማሽነሪዎችን መሰጠቱንም ተናግረዋል።

ስልጠናው በዘርፉ የሚስተዋለውን ጥራት የማስጠበቅ ችግር ከማቃለል ባለፈ ተወዳዳሪነትን ማጎልበትና ኢንቨስትመንቱን ማነቃቃት ላይ የአከናወናቸው ስራዎች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ጠቁመዋል።


 

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት የአረንጓዴ ልማት አግሮ ኢንደስትሪያላዜሽን ተደራዳሪ ቡድን አባል ሜርሲደስ ማሪን ኖርቴስ ህብረቱ ይህን ፕሮጀክት በፋይናንስ መደገፉ እንደሚያኮራው ገልጸዋል።

የቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች ጥራት ለማስጠበቅ የተተገበረው ይህ ፕሮጀክት የአውሮፓ ህብረት በተለይ ወጣቶችና ሴቶች የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆኑና የስራ ዕድል ማስፋት ላይ የያዘውን ሰፊ ዓላማ ለማሳካት ቀጥተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።


 

በመድረኩ የተገኙ የሞጆ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ እሸቱ ሱማ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ ለከተማዋ ለወጣቶችና ለሴቶች ስልጠና በመስጠት እና ማሽነሪዎች በማቅረብ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ ማድረጉ አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ ካሁን ቀደም ይስተዋል የነበረውን የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርት ጥራት ችግር መፍታት ያስቻለ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም