ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።

4ተኛው አመታዊ የናይል ወንዝ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስር ኮንፍረንስ ተካሂዷል።


 

መድረኩ "ቀጣናዊ የኃይል ትስስር ለአካታች እና ዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና Konrad Adenauer Stiftung ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) እንደገለጹት የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት የቀጣናዊ ውህደት እና የትብብር አጀንዳን ለማሳካት ወሳኝ ነው።

የቀጣናው የሀይል ትስስር ለአፍሪካ ሀገራት ሁለንተናዊ እና ለዘላቂ ልማት የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነ አንስተው በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ አስተማማኝ ንፁህ እና ታዳሽ ኃይል ለማቅረብ አበክራ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ ኃይል እያቀረበች መሆኑንና በቀጣይ ለሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ታንዛንያ ለማቅረብ በሂደት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

የአፍሪካውያን ግድብ የሆነው የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቀጣናው በኤሌክትሪክ ኃይል መተሳሰር ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ለዘላቂ ልማት መሳካት ወሳኝ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው ተግባር ለቀጣናዊ ውህደትና የጋራ ብልፅግና መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም ገልጸዋል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራትን በኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

የተለያዩ ጎረቤት ሀገራትን የሚያስተሳስረው በርካታ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ መከናወንን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ይህ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ኢትየጵያን ከሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ጋር ያገናኘ ቀጣናውን በሃይል ብቻ ሳይሆን በህዝብ ለህዝብ ያስተሳሰረ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ አካታች እድገት እና ቀጣናዊ ትስስር ቀጣይነት ባለው እና በአስተማማኝ የኃይል ምንጮች ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሀገር ውስጥ የሃይል አቅምን ከማሳደግ ባለፈ ለቀጣናው ትስስር መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።

ግድቡ ከሃይድሮ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የላቀ መሆኑን ተናግረው፤ ብሄራዊ የአንድነት እና አህጉራዊ የጽናት ምልክት መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም