ብዙአየሁ ብርሃኑ ምስጉን፣ መልካም ስብዕናን የተላበሰ፣ ብቁና ታታሪ የምስልና ድምጽ ቀረፃ ሙያተኛ ነበር - የሥራ ባልደረቦቹ - ኢዜአ አማርኛ
ብዙአየሁ ብርሃኑ ምስጉን፣ መልካም ስብዕናን የተላበሰ፣ ብቁና ታታሪ የምስልና ድምጽ ቀረፃ ሙያተኛ ነበር - የሥራ ባልደረቦቹ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2017(ኢዜአ)፦ ብዙአየሁ ብርሃኑ ምስጉን፣ መልካም ስብዕናን የተላበሰ፣ ብቁና ታታሪ የምስልና ድምጽ ቀረፃ ሙያተኛ እንደነበር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሥራ ባልደረቦቹ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከፍተኛ የምስል ቀረፃ ባለሙያ የነበረው ብዙአሁ ብርሃኑ በሥራ ላይ እያለ ባጋጠመው ድንገተኛ አደጋ ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ትናንት ሰኔ 9/2017 ዓ.ም ህይወቱ አልፏል።
ሥርዓተ ቀብሩም በአዲስ አበባ ተወልዶ ባደገበት ሰፈር በሚገኘው የፈረንሳይ ጉራራ ደብረ-ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን ዛሬ ተፈጽሟል።
ብዙአየሁ ብርሃኑ ከኅዳር 2008 ዓ.ም ጀምሮ ህልፈቱ እስከተሰማበት ድረስ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በከፍተኛ የምስል ቀረፃ ባለሙያነትና በሌሎች ተቋማትም በተለያዩ የሙያ መስኮች ሀገሩን አገልግሏል።
በትምህርት መስክም ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዲፕሎማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።
በሥርዓተ ቀብሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) እና የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ እና ሌሎች የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ተገኝተዋል።
በቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ የብዙአየሁ ብርሃኑ የህይወት ታሪክ በንባብ ቀርቧል።
በኢዜአ የስልጠና ጥናትና ህትመት ማዕከል ኃላፊ ፈለቀ ሽኩር፤ ብዙአየሁ ብርሃኑ ተቋሙ የሚሰጠውን ኃላፊነት በብቃት የሚወጣ ምስጉን ሙያተኛ እንደነበር የህይወት ታሪኩን ባነበቡበት ወቅት ገልጸዋል።
በስራ ዘመኑም ከፍተኛ ኃላፊነትን የሚጠይቁ ጉዳዮችን በምስልና በድምጽ በመሰነድ በሚወደው ሙያው እንደታመነ በተወለደ በ37 ዓመቱ ህይወቱ ማለፉን ገልጸዋል።
በኢዜአ የፕሮዳክሽን ዳይሬክተር አሸናፊ ገብረሥላሴ፤ ብዙአየሁ ብርሃኑ የስራ ታታሪነቱንና ሙያ አክባሪነቱን በሀገር ውስጥና በሌሎች ሀገራት ያስመሰከረ ጠንካራ ሙያተኛ ነበር ብለዋል።
በብዙአየሁ ህልፈት ጥልቅ ሀዘን ለተሰማቸው ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና የሙያ አጋሮቹ መጽናናትን ተመኝተዋል።
በኢዜአ የድረ-ገጽና ማህበራዊ ሚዲያ ቡድን መሪ ጋዜጠኛ ጌትነት ሸንቁጤ፤ ብዙአየሁ ምስልና ድምጽን በጥራትና በብቃት በመሰነድ ስራውን በምክንያትና በቁርጠኝነት የሚሰራ አስደናቂ ሙያተኛ ነበር ብሏል።
ህልፈቱም ከቤተሰቦቹ በተጨማሪ ስራ ባለድረቦቹን፣ ጓደኞቹን የሙያ አጋሮቹን ልብ የሰበረ ድንገተኛ ክስተት መሆኑን ተናግሯል።
በኢዜአ ከፍተኛ አዘጋጅ ጋዜጠኛ የሰራው ወርቁ፤ ኢዜአን ከተቀላቀለበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከብዙአየሁ ጋር በነበራቸው የስራ ስምሪት በአስቸጋሪ ሁኔታ ስራን በብቃት የሚወጣ ብቁ የሙያ አጋር እንደነበር ገልጿል።
የብዙአየሁ ህልፈት ድንገተኛ መሆን አሳዛኝ ነው ያለው ጋዜጠኛ የሰራው፤ የመልካምነት መምህር በሆነው ብዙአየሁ ህልፈት ጥልቅ ሀዘን ለተሰማቸው ሁሉ መጽናናትን ተመኝቷል።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የካሜራ ባለሙያው ሰለሞን ተስፋዬ፤ ብዙአየሁ ብርሃኑ የሙያ አጋር፣ ቅን፣ ሙያውን ወዳድና በርካታ ሰዎችን በማሰልጠን ማብቃት የቻለ ነበር ብሏል።
ብዙአየሁ ያካበተው የሙያ ብቃትና ታታሪነት ለብዙዎች መልካም ስብዕናን ያስተላለፈ ቀና ሰው እንደነበርም ነው የገለጸው።
በሥርዓተ ቀብሩ የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ ጽህፈት ቤቱን በመወከል፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአቶ ብዙአየሁ ብርሃኑ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፤ ለቤተሰቦቹ፣ ለሙያ አጋሮቹና ወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን ይመኛል።