ቀጥታ፡

ፌዴሬሽኑ ለሰላም ግንባታና ልማት ጥረት በማድረግ ለሰው ልጆች ሁሉ ደህንነት መንፈሳዊ ተልዕኮውን ይወጣል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2017(ኢዜአ)፦ ለሰላም ግንባታና ልማት ጥረት በማድረግ ለሰው ልጆች ሁሉ ደህንነት መንፈሳዊ ተልዕኮውን እንደሚወጣ የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው በአፍሪካ የመጀመሪያው የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ትናንት ተጠናቋል፡፡


 

ከዓለም ዙሪያ ካሉ 55 የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን አባል ቤተ ክርስቲያናት ተወካዮች የተሳተፉበት ውጤታማ ስብሰባ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጳጳስ ሄነሪክ ስቱብኬር ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፌዴሬሽኑ የተመሰረተው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1947 ነው፡፡

የፌዴሬሽኑ ዕሴቶች በሰው ልጆች ዘንድ ሁሉ ወንድማማችነት እንዲጎለብት ጥላቻ እንዲርቅ ሰላምን አብዝቶ መስበክ ለልማት ማገዝ ነው ብለዋል፡፡

ለሰላምና ልማት እገዛ እንደሚያደርግ ተቋም በዓለም ዙሪያ ሰላም እንዲሰፍን ልማት እንዲስፋፋ መስራት ይገባል፤ እኛም አብረን እንሰራለን ነው ያሉት፡፡


 

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዝዳንትና የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ቄስ ዶክተር ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው፤ የፌዴሬሽኑ ተልዕኮ የሰላም ንግባታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ለመንግስት የሰላም ጥረት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸው፤ ስብሰባው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኹነቶችን በብቃት የማስተናገድ አቅም እንዳላት ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ዋና ጸሀፊ ቄስ ዶክተር አኔ በርክሀርድት በምክር ቤቱ ስብሰባ በዓለም ዙሪያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ባሉ ሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ የተወያየንበት ውጤታማ ኹነት ነው ብለዋል፡፡

በሰዎች መካከል ትብብርና አንድነት፣ ፍቅርና መተሳሰብ እንዲጎለብት የሰላም ሐዋርያነታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ቄስ አኔ በርክሃርድ፤ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲመጣ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡


 

የታንዛኒያ ኢቫንጀሊካል ሉተራን ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እና የፌዴሬሽኑ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ፕሬዚዳንት ፍሬድሪክ ሾ፤ ስብሰባው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ቀጣና በሆነችው ኢትዮጵያ በመካሄዱ ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም