ቀጥታ፡

አነስተኛ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረጉ ነው

ድሬዳዋ፤ ሰኔ 10/2017(ኢዜአ)፦ በምስራቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተገነቡ አነስተኛ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ። 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚቀጥሉት አምስት አመታት በብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮጀክት በሚተገብራቸው አነስተኛ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ዕቅድ እና አተገባበር ላይ በድሬዳዋ ያዘጋጀው ውይይት ተጠናቋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የዘርፉ አመራሮች ባለፉት አመታት የተገነቡት የአነስተኛ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በየአካባቢው ውጤት እያመጡ ነው ብለዋል።


 

የሶማሌ ክልል ማዕድን፣ ኢነርጂ እና ነዳጅ ቢሮ የኢነርጂ ዳይሬክተር መሐሙድ መሐመድ እንደተናገሩት፤ ባለፉት አመታት በክልሉ  የተገነቡት የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች የክልሉ አርብቶ አደሮችን የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ አስችሏል።

በተለይ ዘንድሮ ሁለት ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የፀሐይ ኃይል ጣቢያ ተመርቆ ወደ አገልግሎት መግባቱ የአርብቶ አደሩን ህይወት በከፍተኛ ደረጃ ለውጦታል ብለዋል።

በዚህም የክልሉ ነዋሪ አሁን ላይ ዘመናዊ ህይወት ከመምራት ባለፈ በኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም በመስኖ ልማት እና በገቢ ማስገኛ ስራዎች ተሰማርቶ ኑሮውን እያሻሻለ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሐረሪ ክልል የኤረር ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ መሐመድ ጀማል በበኩላቸው ባለፉት አመታት በገጠርና በከተማ የተገነቡት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የህብረተሰቡን ማህበራዊ እና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ መለወጥ ችለዋል ብለዋል።

ከብክለት ነፃ በሆነው እና በአነስተኛ ወጪ ተደራሽ በሚሆነው የፀሐይ ኃይል ተጠቃሚ የሆኑ ጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች የተሻለ አገልግሎት መስጠት ማስቻሉንም ገልጸዋል።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ተቋማት መሠረታዊ መፍትሄ ማምጣታቸውን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የኢነርጂ ሃብት ልማት ቡድን መሪ ኢብራሂም አብዲ ናቸው።


 

በዞኑ የተለያዩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበር በ21 ወረዳዎች 110 የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት ከመስጠት በዘለለ በነዳጅ ጀነሬተር የሚከናወኑ የመስኖ ልማቶች ወደ ፀሐይ ኃይል መለወጣቸውን ተናግረዋል።

የዘርፉ አመራሮች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተወጠነው የአምስት አመት ዕቅድ የተገኙትን ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን አንስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም