ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የካሜራ ባለሙያ ብዙአየሁ ብርሃኑ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከፍተኛ የካሜራ ባለሙያ የነበረው ብዙአየሁ ብርሃኑ የቀብር ስነ-ስርዓት በፈረንሳይ ጉራራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ተፈጽሟል።

በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

አቶ ብዙአየሁ ብርሃኑ ከአባቱ ከአቶ ብርሃኑ መኮንን እንዲሁም ከእናቱ ወይዘሮ ጥሩ ታደግ ህዳር 21/1980 ዓ.ም በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ፈረንሳይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወለደ።

ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በመካነ ህይወት ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በከፍተኛ-12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቀለም ትምህርቱን ተከታትሎ አጠናቋል።

በከፍተኛ ትምህርቱም የአድቫንስድ ዲፕሎማ፥ በኤሌክትሮኒክስ ኮምዩኒኬሽን ማኔጅመንት ቴክኖሎጂ በደረጃ-5 ተመርቋል።


 

ሁሌ ራሱን በዕውቀት ማሳደግ የሚወደው ብዙአየሁ የከፍተኛ ትምህቱን በመቀጠል በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በኮምፒውተር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪው አግኝቷል።

በስራው ዓለምም ከሚያዚያ 2004 እስከ 2005 ዓ.ም በጠቅላይ ፍርድ ቤት በድምፅ ባለሙያነት ስራ "ሀ" ብሎ ጀምሯል።

የስራ ትጋትና የመልካም ስብዕና መገለጫ የሆነው ብዙአየሁ ከሐምሌ 2005 እስከ 2007 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ዓመታት በቀድሞው የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በአሁኑ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በካሜራ ባለሙያነት አገልግሏል።

ከኅዳር 2008 ዓ.ም ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈበት ቀን ድረስ ደግሞ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) በከፍተኛ ካሜራ ባለሙያነት ተቋሙንና ሀገሩን በትጋትና በታማኝነት እያገለገለ ነበር።


 

ብዙአየሁ በአብሮ አደጎቹ፣ በስራ ባልደረቦቹ እና በሙያ አጋሮቹ አጠራር “ብዙዬ” በካሜራ የሚጠበብ፣ ካሜራ ይቀርፃል ሳይሆን በካሜራ ስዕል ይስላል የሚባልለት ደከመኝን የማያውቅ ታታሪና ለበርካቶችም አርዓያ የሆነ ባለሙያ ነበር።

በስርዓተ ቀብሩ ላይ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የስራ አመራር ቦርድ አባላት የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአቶ ብዙአየሁ ብርሀኑ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፥ ለቤተሰቦቹ፣ ለሙያ አጋሮቹ እና ለወዳጅ ዘመዶቹ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም