ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሁላችንም የማይደበዝዝ አሻራ ያረፈበት የጋራ ስኬታችን ማሳያ ነው

አሶሳ፤ሰኔ 10/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሁላችንም የማይደበዝዝ አሻራ ያረፈበት የጋራ ስኬታችን ማሳያ ነው ሲሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ምንጭ፣ የቱሪዝም መስህብና የተፈጥሮ ሃብት ማእከል በመሆን የሚያገለግል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ይታወቃል።

ከሀገርም ባለፈ ከአካባቢው አገራት ጋር የኃይል ትስስር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ትርጉም ያለው የልማት ፕሮጀክትም ነው።

በመሆኑም በኢትዮጵያውያን ሃብትና ጉልበት የተገነባው ግዙፉ ግድብ አሁን ግንባታው በመገባደድ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።


 

የህዳሴውን ግድብ ግንባታ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስና ለስኬቱ እየተደረገ ያለውን ተሳትፎ በተመለከተ ኢዜአ በአሶሳ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግሯል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አስናቀች ስጦታው፤ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን የሀገር የልማት ስኬት ማሳያ እና ለሌሎች ስራዎችም የብርታት ምልክት ሆኖ የሚያገለግል ነው ብለዋል።


 

በመሆኑም በእኛው ጉልበትና ጥበብ እንዲሁም የጋራ ጥረት በመገባደድ ላይ በመሆኑ ተደስተናል ሲሉም ተናግረዋል። 

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ እሸቱ ቸኮለ፤ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የጋራ ስኬት ምልክትና የማይደበዝዝ አሻራ በመሆኑ ሁላችንንም የሚያኮራ ነው ብለዋል።


 

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ሙሐመድ ኢብራሂም፤ የውጭ ጫናዎችን እና የውስጥ ችግሮችን በማለፍ ግንባታው በመገባደድ ላይ ያለው ህዳሴ ግድብ ከልማት ስኬትም ባለፈ የኢትዮጵያውያን የድል ምልክትና የታሪክ አሻራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የመንግስት የዲፕሎማሲ ጥረትና የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም ህዝቡ ከዳር ዳር በባለቤትነት መንቀሳቀሱና በተግባርም ማገዙ ለግድቡ ግንባታ መሳካት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታላቁ ሕዳሴ ግድብ  ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ለሜሳ ኔኖ፤ ለሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ለማድረግ በየጊዜው በሚካሄዱ የንቅናቄ ስራዎች ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ከዚህም በተጨማሪ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ እየተከናወነ ባለው የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ የህብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም