በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2017 (ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ የአራተኛ ቀን ውሎ የምድብ 5 እና 6 ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ። 

በምድብ 6 ፍሉሜንሴ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከምሽቱ 1 ሰዓት በሜትላይፍ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ ተገናኝተው አያውቁም። 

ፍሉሜንሴ በፊፋ የክለቦች ውድድር ሲሳተፍ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ቡድኑ እ.አ.አ በ2023 ለፍጻሜ ደርሶ በማንችስተር ሲቲ 4 ለ 0 ተሸንፏል። 


 

ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በውድድሩ ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በምድብ 5 ሪቨር ፕሌት ከኡርዋ ሬድ ዳይመንድስ ጋር ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሉመን ፊልድ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ሪቨር ፕሌት በክለቦች ውድድሩ ላይ ሲሳተፍ የአሁኑ ለሶስተኛ ሲሆን ኡርዋ ሬድ ዳይመንድስ ከዚህ ቀደም የአራት ጊዜ ተሳትፎ አድርጓል። ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በምድብ 6 ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ ኡልሳን ከማሜሎዲ ሳንዳውንስ በኢንተር ኤንድ ኮ ስታዲየም ይጫወታሉ።


 

ኡልሳን በፊፋ የክለቦች ውድድር ላይ ሲሳተፍ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ማሜሎዲ ሳንዳውንስ ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ተሳትፎ አድርጓል። ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ ተገናኝተው አያውቁም።
ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በምድብ 5 ሞንትሬይ ከኢንተር ሚላን በሮዝ ቦውል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ሁለቱ ክለቦች በውድድር ጨዋታ ላይ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። እ.አ.አ በ1994 በወዳጅነት ጨዋታ ተገናኝተው ኢንተር ሚላን 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።



 

ሞንትሬይ ከዚህ ቀደም በፊፋ የክለቦች ውድድር አምስት ጊዜ ተሳትፏል። ኢንተር ሚላን እ.አ.አ በ2010 በነበረው ብቸኛው ተሳትፎ በፍጻሜው ቲፒ ማዜምቤን 3 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም