የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ ተማሪዎች አጥንቼና አውቄ ማለፍ አለብኝ የሚል ተነሳሽነትን በመፍጠር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና አለው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ ተማሪዎች አጥንቼና አውቄ ማለፍ አለብኝ የሚል ተነሳሽነትን በመፍጠር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና አለው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
አዲስ አበባ፣ሰኔ 10/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የትምህርት ፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ተማሪዎች ደክሜ አጥንቼና አውቄ ማለፍ አለብኝ የሚል ተነሳሽነትን በመፍጠር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳለው የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።
የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በስኬት እንዲካሄድ የጸጥታና ባለድርሻ አካላት የጋራ ውይይት አካሒደዋል።
በመድረኩ የፈተና አሰጣጥ መርሃ ግብሩን በሚመለከት በተዘጋጀው የጸጥታ እቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት የተሻለ አገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በዚህ ሂደት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ፣ተደራሽነትን ማስፋትና የትምህርት ስርዓቱን ፍትሃዊና ተአማኒ ማድረግ አንዱና ዋነኛው ስለመሆኑ አንስተዋል።
በመሆኑም ባለፉት ሶስት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ፈተና በአግባቡ እንዲሰጥ የማድረግ ስራ ሲከናወን እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የፈተና አሰጣጥ ችግሮችን በማረም ፈተናውን በተሻለ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ውጤታማ እና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ፈተናውን ከስርቆት በጸዳ መልኩ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም የጸጥታ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ከነበረበት ችግር ተላቆ በተሻለ መልኩ እንዲሰጥ የጸጥታ ተቋማት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘንድሮው ለ150 ሺህ ተማሪዎች ፈተናው በበይነ መረብ እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ፈተና አሰጣጡ ወደ ዲጂታል እንዲሸጋገር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በተሰጡ ፈተናዎች በርካታ ልምዶችን ማግኘት ተችሏል።
በመሆኑም ቀጣዩ የ2017 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ያለምንም ችግር እንዲሰጥ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች በማጠናከሪያ ትምህርት እውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
በራሳቸው የሚተማመኑ ተማሪዎች የማፍራት ራዕይ ለማሳካት የተጀመሩ ጥረቶች ውጤት ማምጣት መጀመራቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መመሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፤ የፈተናው የህትመት ሥራ በሚመለከተው አካል ተጠናቆ አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር ተመልምለው ፈተናውን ለመስጠት ብቁ የሆኑ መምህራንና ባለሙያዎችን ወደ ፈተና ቦታ ማድረስ በቀጣይ የሚከናወን ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።