ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ሰኔ 10/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

4ተኛው  አመታዊ የናይል ወንዝ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስር ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው።

መድረኩ "ቀጣናዊ  የኃይል ትስስር  ለአካታች እና ዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና Konrad Adenauer Stiftung ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።


 

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ኢ/ር) ዶ/ር፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ፤ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት የቀጣናዊ ውህደት እና የትብብር አጀንዳን ለማሳካት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የቀጣናው የሀይል ትስስር ለአፍሪካ ሀገራት ለሁለንተናዊ እና ለዘላቂ ልማት የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነም ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በቀጣናው ተጨባጭ የሆነ የኃይል ትስስር ለመፍጠር  አበክራ እየሰራች ነው ብለዋል።

የአፍሪካዊያን ግድብ የሆነው የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንዱ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።


 

እስከአሁን ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ ኃይል እያቀረበች እንዳለ አንስተው በቀጣይ ይህን በማስፋት ለሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ታንዛንያ ለማቅረብ በሂደት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

የቀጣናው በኤሌክትሪክ ኃይል መተሳሰር ለሥራ እድል ፈጠራ እና ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ለዘላቂ ልማት መሳካት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የኃይል ትስስሩ መሰረተ ልማት ከመዘርጋት በላይ መሆኑን አንስተው፤ ለቀጣናዊ ውህደትና የጋራ ብልፅግና መረጋገጥ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም