ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የካሜራ ባለሙያ ብዙአየሁ ብርሃኑ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ይፈጸማል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 10/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከፍተኛ የካሜራ ባለሙያ ብዙአየሁ ብርሃኑ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ በፈረንሳይ ጉራራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል።

አቶ ብዙአየሁ ብርሀኑ መኮንን በሥራ ላይ እያለ ባጋጠመው ድንገተኛ አደጋ ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ትናንት ህይወቱ አልፏል።

ህዳር 21 ቀን 1980 ዓ.ም የተወለደው ብዙአየሁ ብርሃኑ በስራ ዓለም በጠቅላይ ፍርድ ቤት በድምጽ ቀረጻ ባለሙያነት፣በቀድሞው የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በቪዲዮ ካሜራ ባለሙያነት አገልግሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ከተቀላቀለበት ከህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮም በረዳት ካሜራ ባለሙያነት፣ በካሜራ ባለሙያነትና በመጨረሻም በከፍተኛ የካሜራ ባለሙያነት ሲያገለግል ቆይቷል።

ብዙአየሁ ብርሃኑ በሙያው በሃገር ውስጥና በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመገኘት የሥራ ኃላፊነቱን በሚገባ ሲወጣ የቆየ ምስጉን ባለሙያም ነበር።

የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ፈረንሳይ ጉራራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ይፈጸማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአቶ ብዙአየሁ ብርሀኑ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፥ ለቤተሰቦቹ ፣ለሙያ አጋሮቹና ለወዳጅ ዘመዶቹ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም