ቀጥታ፡

ኪነጥበብ ብሶት ብቻ ሳይሆን ቁጭት ሊፈጥር ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2017(ኢዜአ)፦ኪነጥበብ ብሶት ብቻ ሳይሆን ቁጭት ሊፈጥር ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፥ከመላው ኢትዮጵያ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ከተወጣጡ የጥበቡ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተወካዮች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ችግር ብቻ ሳይሆን ተስፋን በሚያሳዩ ስራዎች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከፖለቲካው ይልቅ ማህበራዊ ጉዳይ ላይ በትኩረት በመስራት የሚያስቡትን ማሳካት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡


 

ኪነጥበብ በመንግስት ብቻ ሳይሆን በባለሙያው መዘከር እንዳለበት እና ኢንዱስትሪው እንዲያድግ ኢትዮጵያ ማደግ እንዳለባት ተናግረዋል፡፡ለዚህም የቱርክ፣የህንድ እና የኮርያን ፊልም ኢንዱስትሪ ለአብነት አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብዙ ባህል ያላት ሀገር መሆኗን በመግለጽ የኢትዮጵያ ኪነጥበብ አድጎ በአፍሪካ እና በዓለም የሚታይ ነገር መፍጠሩ እንደማይቀር አውስተዋል፡፡

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አማካኝነት የህዝብ ለህዝብ መድረክ እየተዘጋጀ መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኪነጥበብ ባለሙያዎች በዋነኛነት አመለካከት ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ኪነጥበብ መዝናኛ ብቻ ሳይሆን ግብ እና ተልዕኮ ያለው መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

መጤ ባህልን መከላከል ብቻ ሳይሆን የተደበቁ ባህሎችን የሚያወጣ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አርቲስት ቋንቋ አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ"አክቲቪስት መሆን ካማረው የአርቲስትነት ካባ እና ክብር እየወደቀ ነው" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል መንግስት የፖሊሲ፣ የአሰራር እና አደረጃጀት ጉዳዮችን ፈትሾ የሚስተካከለውን ለማረም እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

ኪነጥበብ አካታች እና ትውልድ የሚገነባ የጋራ ትርክት ላይ የሚሰራ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

የኪነጥበብ ባለሙያዎች በአንድ ጠንካራ ማህበር መሰባሰብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ተስፋ አላት ትበለጽጋለች ግምት ሳይሆን አቅም አላት" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የምትበለጽገው ችግር ለመቀበል ዝግጁ ከሆንን ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

"ብልጽግናን አይተው ከሚኖሩበት እና ከሚቋደሱት ሰዎች ላልሆን እችላለሁ ነገር ግን የብልጽግናን መሰረት ጥለው ከሚያልፉ ሰዎች አንዱ ነኝ" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ራዕይ እና በችግር ጊዜ ለተሳተፉ የዘርፉ ባለሙያዎች ምስጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ስንበለጽግ በወርቅ አሻራ ስማችሁ የተጻፈ ይሆናል" ብለዋል፡፡

በተቃራኒው "ያኔ ስንፈልጋችሁ የከዳችሁ ይቅር ብለናችኋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ኢትዮጵያን አትካዱ ኢትዮጵያን ክዶ ሃብታም ከመሆን ቢቀር ይሻላል" ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም