ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ ሲፀድቅ የሪልስቴት ዘርፉን የሚያነቃቃ እና ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ሰኔ 9/2017(ኢዜአ)፦የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበት ረቂቅ አዋጅ ሲፀድቅ የሪልስቴት ዘርፉን የሚያነቃቃ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣መሰረተ-ልማትና ትራንስፖርት እና የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የአስረጂ ውይይት አካሂዷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሀመድ አብዶ፥ በረቂቅ አዋጁ ላይ ጥሩ ውይይት መደረጉን ገልጸው፤በአዋጁ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለውጭ ዜጎች ክፍት በመደረጉ የሚመጣ ብዙም ጉዳት እንደማይኖር የሌሎች አገሮች ልምድ በመጥቀስ ጠቁመዋል።

ለመኖሪያ ቤት አቅርቦት የገንዘብ አቅርቦት ችግርን ሊቀርፍ የሚችል አዋጅ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው፤አንድ የውጭ ዜጋ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ከተገኘ ከዜጎች እኩል አገልግልት ማግኘት ይችላል በሚለው ሀሳብ ላይ ገደብና ቅድመ ሁኔታዎች በግልፅ ቢቀመጡ በሚል አንስተዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ሐና አርአያሥላሴ ከቋሚ ኮሚቴዎች አባላት የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራርያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ረቂቅ አዋጁ በዋናነት ቀደም ብሎ የወጣውን የፍትሐብሔር ህግ የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ እንዳይሆኑ የሚከለክለውን አንቀጽ የሚቀይር መሆኑን አንስተዋል።

ረቂቅ አዋጁ አጠቃላይ የሪልስቴት ዘርፉን እድገት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ በዘርፉ ያሉ ፖሊሲዎችን እንደገና በመፈተሽ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ አንዱ እሳቤ ነውም ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁ ሲፀድቅ የውጭ ዜጎች ካፒታል ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ለማበረታታት እና በሀገሪቱ ውስጥ የኢንቨስትመንት ፍሰትን የማሳለጥ ዓላማን የሚያሳካ መሆኑን አስረድተዋል።

በረቂቅ አዋጁ የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበት አግባብ በመኖሪያ ቤት ላይ ብቻ መሆኑን አንስተው፥ ለዚህም አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ዶላር የመነሻ ካፒታል የሚጠበቅባቸው መሆኑን አንስተዋል።

የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ይዞታ ክልከላ እንዲነሳ የተደረገው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የፍትህ ሚኒስቴር እና የከተማ መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በመቀናጀት ጥናት ተደርጎ አዋጭነቱ ታምኖበት እንደተፈቀደ ጠቅሰዋል።

በዚህም የነበረው የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ ክልከላ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ያለበት ኢንቨስትመንት ወደ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት እንዲሄዱ ሲያደርግ መቆየቱ በጥናት መረጋገጡን አንስተዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፥ አሁን በሃገሪቱ ያለው የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ከፋይናንስ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስትም ይህን ችግር ለመቅረፍ የሪልስቴት አዋጅ ከማጽደቅ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁ የውጪ ምንዛሪ እንዲጨምር በማድረግ ያለውን የፋይናንስ ችግር ከመቅረፍ ባለፈ የቤት አቅርቦትን ለመጨመር ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለዚህም ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ፥ አብዛኞቹ የተነሱ ሃሳቦች በግብዓትነት እንደሚወሰዱ ገልፀው፤ ረቂቅ አዋጁ ሲፀድቅ የቤት አቅርቦትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምረው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም