ቀጥታ፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ምሁራን የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው-የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 9/2017(ኢዜአ)፦ኮሚሽኑ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ምሁራን የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ ጥሪ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በምክክር ሂደቱ ዙሪያ ግብዓት ለማሰባሰብ እና ይበልጥ ተቀራርቦ መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ከምሁራን ጋር ተወያይቷል።

የመድረኩ ተሳታፊ ምሁራን የእስካሁኑ የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸው ምልከታ እና በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች በአጀንዳ ቀረጻ፣ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ፣እንዲሁም በምክረ ሀሳብ ዝግጅት ዙሪያ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።

እንዲሁም ምክክር ኮሚሽኑ በቀጣይ የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ድጋፍ እና ትብብር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ ኮሚሽኑ ባለፉት አመታት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ሀገራው ምክክር ጉባኤ የሚካሄድበትና አጀንዳ የሚቀረፅበት ወቅት የተቃረበበት ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደት ምሁራን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ምሁራን በምክክር ሂደቱ እንዲካተቱና ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ምሁራን በአጀንዳ ልየታ ሕዝባዊ መድረኮች እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ከማመቻት ባለፈ አሉን የሚሏቸውን አጀንዳዎች በቀጥታ ለኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

ከውይይት ተሳታፊዎች መካካል አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን ድረስ በአጀንዳ አሰባሰብ ያከናወናቸው ተግባራት የሚያስመሰግንና ለሀገሪቱ ትልቅ ውለታ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ያሉ ስራዎች የሁሉንም አካላት ድጋፍ የሚፈልግ በመሆኑ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው ተሳታፊ አብዲሳ ዘርዓይ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት አመታት ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረው፤ በቀጣይ ስራዎች የምሁራን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በትኩረት መሳተፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም