የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ፖሊሲ ለእርጥበታማና ውሃ አዘል አካባቢዎች ደኅንነት አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው-የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ፖሊሲ ለእርጥበታማና ውሃ አዘል አካባቢዎች ደኅንነት አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው-የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን
አዲስ አበባ፤ሰኔ 9/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ፖሊሲ ለእርጥበታማና ውሃ አዘል አካባቢዎች ደኅንነት አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።
በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የእርጥበታማ አዘል መሬት ጽሕፈት ቤት (Wetlands International Ethiopia office) ያዘጋጀው የእርጥበታማ አዘል መሬትን የመንከባከብና መልሶ እንዲያገግም የማድረግ ስትራቴጂካዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የኢትዮጵያ አካባባቢ ጥበቃ ባስልጣን፣ለጋሽ ድርጅቶች፣የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮችና የዘርፉ ምሁራን ተሳትፈዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጠን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ እርጥበታማ የሥነ-ምኅዳር አካባቢዎች ለብዝኃ ሕይወት ደኅንነት ወሳኝ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም እርጥበታማ አካባቢ ለብዝኅ-ህይወት ደህንነት መሰረት መሆናቸውን በመገንዘብ የልማት አጀንዳ አካል በማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም እርጥበታማ አካባቢዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃብት አካል በማድረግ መጠበቅና መንከባከብ የሚያስችል ፖሊሲ በመቅረጽ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተጣጣመ የእርጥበታማ አካባቢ ልማት እየተከናወነ እንዲሁም እርጥበታማ አካባቢዎችን የሚከታተል የስራ ክፍል በማዋቀር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
እየተተገበረ ያለው ፖሊሲ ለእርጥበታማና ውሃ አዘል አካባቢዎች ደኅንነት አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የእርጥበታማ አዘል መሬት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኮራድ ክራይገር በበኩላቸው፥ ኢትየጵያ በሥነ-ምኅዳር ጥበቃ አስደናቂ ስራ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
ኢትየጵያ እየሰራች ባለው የሥነ-ምኅዳር ጥበቃ በደን ልማት በንብ ማነብና ሌሎች የስራ ዕድል መስኮች ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን እርጥበታማ አካባቢዎች ሥነ-ምኅዳራዊ ድኅንነት ለመጠበቅ እየሰራችው ላለው ውጤታማ ስራ የባለድርሻ አካላት ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የዓለምአቀፍ የእጥበታማ አዘል መሬት ጽሕፈት ቤትም የእርጥበታማና ውሃ አዘል አካባቢዎችን ሥነ-ምህዳራዊ ድህንነት ለመጠበቅ የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የዊትላንድ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ፕሮግራም አስተባባሪ የዶክተር ስሜነህ ሽፈራው በበኩላቸው፤ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ለውሃአዘል መሬቶች በቂ ትኩረት እንዲሰጣቸው እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡