በምክር ቤቱ የህገ መንግሥት ትርጉም የተሰጠባቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የፍትህ አካላት ሚና ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በምክር ቤቱ የህገ መንግሥት ትርጉም የተሰጠባቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የፍትህ አካላት ሚና ሊጠናከር ይገባል

አዳማ፤ ሰኔ 9/2017(ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግሥት ትርጉም በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የፍትህ አካላት ሚና መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ጋር በመተባበር በሕገ መንግስት ትርጉም እና ውሳኔ አፈጻጸም እንዲሁም በፌዴራሊዝም ስርዓት ዙሪያ ከፍትህ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በመድረኩ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የህግ አማካሪዎች እና የክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ፍርድ ቤት ዳኞች ተገኝተዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግሥት ትርጉምና የውሳኔዎች አፈፃፀም ቋሚ ኮሚቴ ፀሓፊ ወይዘሮ ፍሬህይውት ዱባለ፤ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 62 መሰረት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስት የመተርጎም ስልጣን የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።
የህገ መንግስት ትርጉም የሚሰጠውም ህገ መንግስታዊ ክርክር በሚነሳበት ወቅት በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም የህገ መንግሥት ትርጉም በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በምክር ቤቱ አማካኝነት ውሳኔዎች እየተሰጡ መሆኑን አንስተው ከውሳኔዎቹ ተፈጻሚነት አንጻር የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይም ከህገ መንግስት ትርጉም ጋር ተያይዞ በአፈጻጸም ላይ የሚያጋጥሙ ችግርችን ለመቅረፍ የፍትህ አካላትን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት አመልክቷል።
የዛሬው መድረክም የመንግስት አካላት፣ የፍርድ ቤቶችና በሂደቱ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ለይተው ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የፍትህ አካላት በየዕለቱ በሚሰጡት ውሳኔ ውስጥ የተሻለ ክህሎትና ዕውቀት እንዲጨብጡ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
በምክር ቤቱ የህገ መንግሥት ትርጉም የተሰጠባቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የፍትህ አካላት ሚና ሊጠናከር ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዳይሬክተር ሃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዜጎች በዕኩልነት ፍትህ እንዲያገኙ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።
በተለይ የፍትህ አካላት በየዕለቱ በስራቸው የሚያጋጥማቸውን የህግ ክፍተቶች ለመሙላት በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በጥቅሉ ጠንካራ የፌዴራል ስርዓት ለመገንባት የፍትህ ዘርፉ ሕገ መንግስቱን ማዕከል ባደረገ መልኩ ዜጎችን ተጠቃሚ የማድረግ ሚና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።