በምእራብ እና ደቡብ ምእራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ከመደበኛው በላይ ዝናብ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በምእራብ እና ደቡብ ምእራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ከመደበኛው በላይ ዝናብ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2017 (ኢዜአ)፦በምእራብ እና ደቡብ ምእራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ በኬኒያ፣ ኡጋንዳ እና በምስራቃዊ የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች ከመደበኛው በላይ ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት አስታወቀ።
ከሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በቀጣዮቹ ስምንት ቀናት በምስራቅ አፍሪካ የሚኖረውን የአየር ሁኔታ በተመለከተ የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት (ኢክፓክ) ትንበያውን አስቀምጧል።
በምእራብ ኢትዮጵያ፣ ምእራባዊ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ምስራቃዊ ክፍል የአየር ሁኔታው ሞቃታማ መሆኑ ተመላክቷል።
በዚህም መሰረት በምእራብ እና ደቡብ ምእራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ በማእከላዊ እና ምእራባዊ ኬኒያ፣ በኡጋንዳ በርካታ አካባቢዎች፣ በምስራቃዊ ደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሰሜንና ደቡባዊ የሶማሊያ ግዛቶች ከመደበኛው በላይ ዝናብ እንደሚኖር ተገምቷል።
በመሆኑም በእነዚህ አገራት ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ከወዲሁ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው በመረጃው ተመላክቷል።
በኡጋንዳ ደቡባዊ ክፍል፣ በኬኒያ ጠረፋማ እና ሰሜን ምእራብ የአገሪቱ ክፍሎች፣ በሰሜንና ደቡብ ሶማሊያ እንዲሁም በማእከላዊና በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍሎች ደግሞ መጠነኛ ዝናብ ሊኖር ይችላል ተብሏል።
በቀጣዮቹ ቀናት በኢትዮጵያ የአፋር ክልል፣ በደቡብ ምስራቅ ሱዳን፣ በጅቡቲ እና በኤርትራ ጠረፋማ ስፍራዎች የአየር ሁኔታው ሞቃታማ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑ ተጠቁሟል።