ቀጥታ፡

በመጪዎቹ አምስት አመታት 1 ሚሊዮን የሚጠጋ የገጠሩን ማህበረሰብ የታዳሽ የሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ድሬደዋ፣ሰኔ 8/2017 (ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አምስት አመታት በብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮጀክት 1 ሚሊዮን የሚጠጋ የገጠሩን ህብረተሰብ የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሶማሌና የሐረሪ ክልሎች፣የኦሮሚያ ክልል የምስራቅ እና የምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮጀክት አተገባበር እና ቀጣይ ስራዎች ላይ በድሬዳዋ ውይይት ተካሄዷል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሌ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ከዋና ዋና የኤሌክትሪክ መስመሮች ርቀው የሚኖሩ የገጠሩ ህብረተሰብ ክፍሎችን የፀሐይና የንፋስ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው።

የአነስተኛ የፀሐይ ሐይል ማመንጫዎች ውጤታማነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮጀክት ተነድፎ ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል።

በዚህ የታዳሽ ኃይል ሃብቶችን ወደ ጥቅም ለመለወጥ በተቀየሰው ፕሮጀክት በመጪዎቹ አምስት አመታት 240 ሺሀ ቤተሰቦች፣ በተበታተነ መንገድ የሚኖሩ 751 ሺህ ግለሰቦች፣1400 የገጠር ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማትን ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፥ የፕሮጀክቱ መተግበር አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የተፈጥሮ ፀጋዎችን በመጠቀም የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ ያግዛል።

ለፕሮጀክቱም መሳካት የክልሎቹ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል የድሬዳዋ አስተዳደር ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፉአድ መሐመድ በበኩላቸው፥ የታዳሽ ኃይል ሃብቶችን ወደ ጥቅም በመለወጥ በተከናወኑ ስራዎች የገጠሩን ህብረተሰብ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በተለይ የአነስተኛ የፀሐይ ሐይል ማመንጫዎችን ለመስኖ ስራ ጭምር በመጠቀም የገጠሩ ህብረተሰብ ምርታማነት እንዲጨምር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም