ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ስምና ክብር በዓለም ከፍ ለማድረግ ሊተጋ ይገባል-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ስምና ክብር በዓለም ከፍ ለማድረግ ሊተጋ ይገባል-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 8/2017(ኢዜአ)፦ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ፣ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር የኢትዮጵያን ስምና ክብር በዓለም ከፍ ለማድረግ ሊተጋ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለፁ።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባቸውን 22 ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፥ በፕሮጀክቶቹ የምርቃት መርኃግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ለአንድ ምዕተ ዓመት ለአካባቢው ማህበረሰብ የህክምና አምባ፣ የመዳንና የመጠገን ምልክት ከመሆኑም ባሻገር ስመጥር ባለሙያዎችን ያፈራ የልህቀት ማዕከል መሆኑን ተናግረዋል።
ከ70 ዓመታት በፊት የተለኮሰው የዩኒቨርሲቲው የእውቀትና የትምህርት ጉዞ ደግሞ ለሀገራችን መድህን የሆኑ መፍትሔዎችንና ዜጎችን ማፍለቅ መቻሉን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲተው ከ10 ዓመት በፊት ከሚያውቁት የላቀና የሚያኮራ ለውጥ ማስመዝገቡንም አንስተዋል።
ስኬቱም የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የማህበረሰቡ በሥራ የመግባባት ያመጣው መሆኑን በማንሳት፥ የጀመረውን የዘመናዊነት ፈር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።
የጎንደር ማህበሰብ ለዩኒቨርሲቲው ያለው ልዩ የባለቤትነት ስሜትና ለኢትዮጵያውያን የአንድነት ጉዞ ልዩ ምሳሌ የሚሆንና የስኬቱ ሚስጢር እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ማህበረሰቡ ለተቋሙ ቀጣይነት ያለው ለውጥ የሰጡት ትኩረት ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት የመሸጋገር የዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ ሆኖ የጀመራቸው ሥራዎች ተቋሙን ወደላቀ ከፍታ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ፣ ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን በማስፋትና ሀገር ወዳድ ሙያተኞችን በማፍራት የኢትዮጵያን ስምና ክብር በዓለም ከፍ የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲያጠናክርም የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዛሬ የተመረቁ ፕሮጀክቶች መነሻ እንጂ መዳረሻ ባለመሆናቸው ለበለጠ መትጋት እንደሚገባም እንዲሁ።