ቀጥታ፡

ቤተሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ የመዲናዋን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ራዕይ ያግዛል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 8/2017(ኢዜአ)፦ቤተሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ የመዲናዋን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ራዕይ የሚያግዝ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሶስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ወጭ የተገነባውን የቤተሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ መርቀዋል፡፡

ከንቲባዋ በመርሀ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ተስማሚና ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት የሚያሳድጉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የላቀ አገልገሎት መስጠት የሚያስችሉ የቱሪዝም፣የጤናና የመንገድ ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ራዕይ አለን ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ለራዕዩ መሳካት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የቤተሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ ደስ ብሎኛል ያሉት ከንቲባዋ፤በአፍሪካ የመጀመሪያው የልብ ህክምና መሳሪያ የተገጠመለት መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአጥንት መመርመሪያ መሳሪያ የያዘ፤ በኢትዮጵያ የላቀ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ለውጭ ሀገር ህክምና የሚወጣውን ምንዛሪ የሚያስቀር፤ ለሜዲካል ቱሪዝም የጎላ አበርክቶ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርግ በመጥቀስ፣ ፍላጎት ያላቸውን አልሚዎች ግማሽ መንገድ ሂዶ ይቀበላቸዋል ብለዋል።

አዲስ አበባ በፍጥነት እየተቀየረች በመሆኑ ለቤተሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ ምዕራፍ ሁለት ግንባታ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

የቤተሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አየለ ተሾመ በበኩላቸው፥ ሆስፒታሉ ዓለም በህክምና አገልግሎት የደረሰበትን ለመስጠት የተዘጋጀ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ደረጃ በቴሌ ሜዲስን፣በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በርቀት ህክምና ዘመናዊና የሚለካ ህክምና መስጠት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት በመደገፍ የሜዲካል ቱሪዝምን ማስፋፋት የሚያስችል፤ ኢትዮጵያውያን ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር ሲሄዱ የሚደርስባቸውን እንግልትና ወጭ የሚቀንስ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
#Ethiopian_News_Agency
#ኢዜአ
#Ethiopia

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም