የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽና ምቹ ከማድረግ አንጻር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽና ምቹ ከማድረግ አንጻር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 8/2017(ኢዜአ)፦የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽና ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን አሳሰበ።
የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ስራ እየሰሩ ነው።
ለአብነትም የአዲስ አበባ ዩንቨርሰቲ እና ጎንደር ዩንቨርሲቲዎች አርአያ የሚሆኑ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ተሞክሮ በመውሰድ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠውን ትኩረት በማጠናከር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
አቶ አባይነህ እንደገለጹት፥ አካል ጉዳተኞች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚቀላቀሉበት ወቅት በተለይም ከመሰረተ ልማት አንጻር ችግር እየገጠማቸው ይገኛል።
ከሚያጋጥማቸው ችግሮች መካከልም የመመገቢያ፣የመማሪያና የማደሪያ ክፍሎችና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽና ምቹ አለመሆን ዋነኛው ችግር ነው ብለዋል።
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በጥቂት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሻለ ሁኔታ ቢኖርም አብዛኛዎቹ በዚህ ልክ ባለመሆናቸው በቀጣይ በትኩረት ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ግንባታ ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ በረከት ተዘራ፥ በበጀት አመቱ የወጣው የህንጻ አዋጅ 1356/2017 መሰረተ ልማቶች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ተገቢውን ትኩረት የሰጠ ነው ብለዋል።
የአካል ጉዳተኞችን አካታችነትና መሰረተ ልማት ተደራሽነት ላይ ያተኮረ መመሪያ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሰራጭ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተለይም መመሪያው ከተሰራጨ በኋላ የግንባታ ፍቃድ ከሚሰጥበት አንዱ መመዘኛ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ የዲዛይን ዝግጅት መሆኑን አንስተዋል።
ቀደም ሲል የተገነቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ያሉትን ችግሮች ለማየት ጥረት አድርገናል ብለዋል።
ለአብነትም የዲላና የጂንካ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በቢሾፍቱ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸውን በማየት የዲዛይን ክለሳ እና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉን ተናግረዋል።
አቶ በረከት እንደገለጹት፥ አዲስ የሚገነቡ ተቋማት በቅድመ ግንባታ ወቅት ከዲዛይን ጀምሮ ቁጥጥር የሚደረግ ሲሆን ቀደም ሲል በተገነቡት ላይም አካል ጉዳተኞችን ባማከለ መልኩ የእድሳት ስራ እንዲሰራ ለማድረግ እቅድ ተይዟል።
በአጠቃላይ የግንባታ ስራዎች የጥገና እና እድሳት ስራዎች በጀት በመያዝ እንዲከናወኑ የማድረግ ስራዎችን ላይ ለመስራት መታቀዱንም ጠቁመዋል።