የቁም እንስሳት ኳረንቲን ማእከላትን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው -የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የቁም እንስሳት ኳረንቲን ማእከላትን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው -የግብርና ሚኒስቴር
አዳማ፤ሰኔ 8/2017 (ኢዜአ)፦በአርብቶ አደሩ አካባቢ የቁም እንስሳት ኳረንቲን ማእከላትን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።
ሚኒስቴሩ በቦረና ዞን ሞያሌና በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ቦርደዴ ለሚገነባው የቁም እንስሳት ኳረንቲን ማእከል ስኬት ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ግርማ ሙሉጌታ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፥ የቁም እንስሳት ኳረንቲን ማእከል ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ይህም ጥራት እና ጤንነቱ የተረጋገጠ የቁም እንስሳት ለውጪ ገቢያ ማቅረብ ከማስቻሉም በላይ አርብቶ አደሩ ከእንስሳት ሀብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
የቁም እንስሳት ኳራንቲን በህገወጥ መንገድ ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት ንግድ ለመከላከል እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
አሁን በኦሮሚያ ክልል ሞያሌና ቦርደዴ የሚገነቡት የቁም እንስሳት ኳረንቲኖች ቀደም ሲል በሚሌ የእንስሳት ኳረንቲን ይደረግ የነበረን የቁጥጥር ስራ ያጠናክራሉ ብለዋል።
የቦርደዴ ኳረንቲን እንስሳቱ ጥራት፣ጤንነታቸውና ደህንነታቸውን በጠበቀ መልኩ በባቡር ወደ ጂቡቲ ወደብ ለማድረስ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሃሚድ ጀማል በበኩላቸው፥ የቁም እንስሳት ኳረንቲን ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚሌ ኳረንቲን ማዕከል ወደ ተቀባይ ሀገራት የሚላኩ የቁም እንስሳት ደህንነትና ጥራታቸው ተጠብቆ ወደ ውጭ በመላክ ከዘርፉ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
አዲስ የሚገነቡት የሞያሌና የቦርደዴ ኳረንቲን ማዕከላት ጥሩ የመውጫ በሮች በመሆናቸው የቁም እንስሳቱን ጥራትና ጤንነቱን በጠበቀ መልኩ ለውጪ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ ለቁጥጥርና ክትትል አመቺ አሰራር የሚፈጥሩ መሆኑንም ተናግረዋል።