ለደብረ ማርቆስ ከተማ ልማት መፋጠን የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለደብረ ማርቆስ ከተማ ልማት መፋጠን የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው

ደብረ ማርቆስ ፤ሰኔ 8/2017(ኢዜአ)፦የደብረ ማርቆስ ከተማን ልማት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ድርሻ ወሳኝ መሆኑን የከተማዋ መሰረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
በከተማ አስተዳደሩ መሰረተ ልማት መምሪያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ ዲያቆን ሰለሞን ይግረም እንደገለጹት፥ ማህበረሰቡ በአካባቢው ልማት የሚያደርገው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
በበጀት አመቱ እስካሁን ህብረተሰቡ በከተማዋ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከ69 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፥ ከዚህ ውስጥ 41 ሚሊዮን የሚሆነው በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ የተደረገ ነው ብለዋል።
ከተከናወኑ የልማት ስራዎች ውስጥም የ3 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ ፣ የ1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የማፋሰሻ ቦይ፤ ሁለት ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታና ሌሎች ይገኙበታል።
በተጨማሪም ከ140 በላይ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና እድሳት በማካሄድ የልማት ስራዎቹ ሰው ተኮር እንዲሆኑ ጥረት መደረጉን አስገንዝበዋል።
በከተማው ለሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በጥሬ ገንዘብ፣ በጉልበትና በቁሳቁስ አቅርቦት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የቀበሌ 8 ነዋሪ ወይዘሮ ትብለጥ ፈረደ እንደገለጹት፥ የአመታት የልማት ጥያቄያቸውን የመለሱ የጌጠኛ ድንጋይ ማንጠፍ ስራና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ ከተማዋን ለስራና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን ማድረጉን ጠቅሰዋል።
እሳቸውም ለከተማዋ ልማት መፋጠን የበኩላቸውን ገንዘብ ማዋጣታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም በከተማ አስተዳደሩ የተገነቡ የመሰረተ ልማቶች የአካባቢውን ማሀበረሰቡን በማስተባበር እንዲጠበቁና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ታምሩ ደነቀው እንደገለጹት፥ ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች ስኬታማነት በሃሳብ፣ በገንዘብና በጉልበት እያገዙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተለይም በከተማዋ እየተገነባ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ በመቀየሩ ለልማቱ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረን ብለዋል።