የመውረድ ስጋት ያንዣበባቸው ክለቦች የሚያደርጓቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመውረድ ስጋት ያንዣበባቸው ክለቦች የሚያደርጓቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2017(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ35ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ፋሲል ከነማ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ፋሲል ከነማ በ41 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። በ34ኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመርታት ከስምንት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።
ባለፉት አራት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በ38 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ የመቆየት እና ያለመቆየት እጣ ፈንታ የመወሰን ትልቅ አቅም አለው።
በተመሳሳይ ከቀኑ 9 ሰዓት በወንጂ ሁለገብ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ 70 እንደርታ ይጫወታሉ።
ከሊጉ የወረደው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ19 ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃን ይዟል። መቀሌ 70 እንደርታ በ38 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም የግድ ሶስት ነጥብ ማግኘት ይኖርበታል።
መቻል ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀኑ 9 ሰዓት ቢሾፍቱ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ባለፉት ስምንት የሊጉ ጨዋታዎች ያላሸነፈው መቻል በ44 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ38 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመውረድ ለመትረፍ ጨዋታን ማሸነፍ እና ሶስት ነጥብ መጨበጥ ይኖርበታል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወላይታ ድቻ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ባለፉት ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ40 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ በሊጉ የመቆየት እድሉን የበለጠ ያሰፋዋል።
በ45 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ጨዋታው ደረጃውን ከማሻሻል የዘለለ ትርጉም የለውም።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ35ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ላይ የክለቦችን ውጤት እና የመጫወቻ ሜዳዎች ያሉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ማሻሻያ ማድረጉን የሊጉ አክሲዮን ማህበር መግለጹ የሚታወስ ነው።