የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ደህንነትን በማረጋገጥ ለግንባታው አስተዋጽኦ እያደረግን ነው - የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ደህንነትን በማረጋገጥ ለግንባታው አስተዋጽኦ እያደረግን ነው - የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና አባላት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደህንነትን በማረጋገጥ ለግንባታው በተለያየ መልኩ አስተዋጽኦ እያደረገን ነው ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና አባላት ገለጹ።
የመላው ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ደረጃ ላይ መድረሱ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።
በምዕራብ ዕዝ የሕዳሴ ኮር ሶስተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን "ሕዳሴን በሕዳሴ ኮር" በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ላይ ይገኛል።
የሠራዊቱ አባላትም በዛሬው ዕለት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም የመላው ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ወደ መጠናቀቁ ደረጃ ደርሶ በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሙላቱ ጀልዴ በጉብኝቱ ወቅት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወደ መጠናቀቁ ደረጃ ለመድረሱ መላው ኢትዮጵያውያን ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
መከላከያ ሠራዊቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን እንዲሆን የግድቡን ደህንነት ከማስጠበቅ ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።
በምዕራብ ዕዝ የሪጅን ሶስት ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል እዘዘው መኮንን እንደገለጹት፤ ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና ግዳጁን በብቃት ለመወጣት ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ ነው።
ሕዳሴ ኮር የግድቡን አካባቢ ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር እያደረገ ያለውን ተግባር በውጤታማነት እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በምዕራብ ዕዝ የ403 ኮር አባል ሌተናል ኮሎኔል ፍሰሃ ጥላሁን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያውያን እስትንፋስ በመሆኑ ሠራዊቱ ሁሌም የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ታላቁ የሕደሴ ግድብ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሠራዊቱ አስፈላጊውን ሁሉ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
ዛሬ ለደረሰበት የመጠናቀቅ ደረጃ ደርሶ በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በምዕራብ ዕዝ የ403 ኮር አባል ሌተናል ኮሎኔል ቴዎድሮስ ዘመነ እንዳሉትም፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የይቻላል መንፈስ ማሳያ ነው።
ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለሀገር በረከት የመሆን ደረጃ ላይ በመድረሱ መደሰታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።