ሴቶች በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ ሴቶች በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ ”ኢትዮጵያ ትገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ ሴቶች በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያላቸው ተሳትፎ ማዳበር በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ የሚመክር ኮንፍረንስ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሴት አመራሮች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊ ቤዛዊት ግርማ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በኢትዮጵያ ሴቶች በተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶችና መሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች ጉልህ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ።

 በአሁኑ ወቅትም ዘርፉ በቴክኖሎጂ እያደገ በመምጣቱ በአገሪቱ የልማት ጉዞ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል። 

ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ህጎች ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ሴቶች በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ ለማድግ  በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሴቶች በግንባታ ዘርፍ ያለውን እድልና ቴክኖሎጂ በመጠቀም እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በማዳበር ወደ ዘርፉ በስፋት መግባት እንዳለባቸውም አስታውቀዋል።

ሴቶች በኮንስትራክሽን ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ዶክተር ቤዛዊት ያስታወቁት።


 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ፍቅር አባይ በዚሁ ግዜ  በአገሪቱ በሚከናወኑ  ትላልቅ  ፕሮጀክቶች ላይ የሴቶችን  ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል ።

ይህንንም ለማጠናከር የህግና ፖሊሲ ክፍተቶች ከመሙላት አኳያ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።


 

በኮንስትራክሽን ስራ ላይ የተሰማሩ መንግስታዊና የግል ድርጅቶችም የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ወሳኝ ድርሻ አላቸው ያሉት ደግሞ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ነጭቴ ፍላቴ ናቸው።

የሴቶችን እኩል ተሳታፊነት የተመለከቱ ረቂቅ አዋጆች ፀድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ የድርሻቸው እንደሚወጡም ተናግረዋል።


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና በመድረኩ ጥናት ያቀረቡት ደጅይጥኑ አለነ እንዳሉት ሴቶችን በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ ለማሳደግ አቅዶ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

በሀገሪቱ እየተከናወኑ በሚገኙ የኮሪደር ልማት የሴቶች ተሳትፎ የተሻለ በመሆኑ ይህም ለሌሎች ዘርፎች ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም