የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በበይነ መረብ ለመፈተን የሚያስችል በቂ ልምምድ አድርገናል-በአዲስ አበባ ተፈታኝ ተማሪዎች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በበይነ መረብ ለመፈተን የሚያስችል በቂ ልምምድና ዝግጅት ማድረጋቸውን በአዲስ አበባ  የዘንድሮ  ተፈታኝ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ ለተፈታኝ ተማሪዎች በበይነ መረብ ለሚሰጠው ፈተና የመጨረሻ የልምምድ  ፈተና ዛሬ ተሰጥቷል፡፡


 

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሀምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚሁ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች እንደተናገሩት በበይነ መረብ ለሚሰጠው ፈተና በቂ ልምምድ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ፈተናው በበይነመረብ መሰጠቱ በቀጣይ ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን ቴክኖሎጂን ይበልጥ እንዲለማመዱ እድል የሚሰጥ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ዮርዳኖስ ፍቃዱ እንዳለችው ፈተናው በበይነ መረብ  መሰጠቱ ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን የቴክኖሎጂ እውቀትን ለማዳበር ትኩረት እንድንሰጥ ያስችለናል ብላለች።

ፈተናውን በራሳችን ዝግጅት ላይ ተመስርቶ በመስራት የጥረታቸንን ዋጋ እንድናገኝ በማድረግ በኩል ትልቅ ጠቀሜታ አለው ያለችው ደግሞ ተማሪ  ሜሮን እንዳለ ነች።


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ተማሪ ናታኒም ኤሊያስ እንዳለችው፤ በዛሬው እለት የወሰዱት የመጨረሻ የልምምድ ፈተና ለዋናው ፈተና ብቁ እንዲሆኑ ሚያስችላቸው መሆኑን ነው የገለጸችው፡፡


 

ተማሪዎቹ በበይነ መረብ ለሚሰጠው ፈተና በቂ ዝግጅት ለማድረግ በዛሬው እለት የመጨረሻ የልምምድ ፈተና በመፈተን ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተናግራለች።


 

በልምምድ ወቅት መምህራኖቻቸው የተለያዩ  ጥያቄዎችን በማዘጋጀት ለፈተናው እንዲዘጋጁ የሚጠበቅባቸውን ሲያደርጉ እንደነበር የገለጸው ደግሞ ተማሪ ዳግማዊ ታደሰ ነው፡፡

በዛሬው እለት ያደረጉት የመጨረሻ የልምምድ ፈተናም ክፍተቶቻቸውን ለይተው በማስተካከል ለዋናው ሀገር አቀፍ ፈተና እንዲዘጋጁ ያሚያደርጋቸው መሆኑን ተናግሯል፡፡ 


 

የመጨረሻው ልምምድ ለዋናው ፈተና ያደረኩትን ዝግጅት ለመፈተሽ ያስቻለኝ  ነው ስትል የገለጸችው ደግሞ ተማሪ ዮርዳኖስ አበበ ነች፡፡


 

ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ልምምዶችን እና በቂ ዝግጅት በማድረግ ሀገር አቀፍ  ፈተናውን በመጠባበቅ ላይ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ተማሪ አቤኔዘር ፍቃዱ ነው፡፡ 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም