ዜጎች ደምና የዓይን ብሌን በመለገስ የሚያበረክቱትን በጎ ተግባር አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዜጎች ደምና የዓይን ብሌን በመለገስ የሚያበረክቱትን በጎ ተግባር አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ዜጎች ደምና የዓይን ብሌን በመለገስ የሚያበረክቱትን በጎ ተግባር አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የደም እና የዓይን ብሌን ለጋሾች ቀን በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በመርሀ ግብሩ ላይ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየዳበረ ሲሆን በህብረተሰቡ ዘንድም ደም መለገስ እየተለመደ ነው።
ይሁን እንጂ ደም የመለገስ ተግባር ወጥነት እንደሌለው ያነሱት ዶክተር መቅደስ፤ በዘመቻና በንቅናቄ ተግባራት ላይ መመስረቱ ውስንነት እንዲያጋጥመው አድርጎታል ብለዋል።
ህብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ደም የመለገስ ተግባርን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያከናውንም ጥሪ አቅርበዋል።
ይህም በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰት የእናቶች ሞት ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረት ከዳር ለማድረስ አይነተኛ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
በተለያየ የጤና እክል ምክንያት በቋሚነት ደም ለሚያስፈልጋቸው፣ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋ የደም እጥረት ለሚያጋጥማቸው ሰዎችም የደም አቅርቦት ወሳኝ በመሆኑ ደም የመለገስ ልምዱ እየተጠናከረ መሄድ እንዳለበት ጠቁመዋል።
መንግስት የደም ባንኮችን፣ የህክምና ተቋማትንና መሰል ግብዓቶችን በማሟላት ረገድ እያከናወነ ባለው ተግባር አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ገልጸዋል።
የጤና አገልግሎትን ወጥና ተደራሽ ለማድረግ ዜጎች ደምና የዓይን ብሌን በመለገስ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ነው ዶክተር መቅደስ የገለጹት።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው፤ አንድ ሰው ደምና የዓይን ብሌን በሚለግስበት ወቅት ተስፋን፣ የወደፊት ብርሀንና ህይወትን መስጠት መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህም ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ መሆኑን ነው የገለጹት።
በመረሀ ግብሩ ላይ በተከታታይ ደም የለገሱ ሰዎች እውቅና የተ
ሰጣቸው ሲሆን፤ ሰዎች ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌንን እንዲለግሱ ጥሪ የሚቀርብበት ነውም ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰኔ ወር እየተከበረ ያለው 21ኛው የደምና የዓይን ብሌን ለጋሾች ቀን "የሕይወትና የብርሀን ስጦታ! ደም ይለግሱ፤ ብሌንዎን ቃል ይግቡ" በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተከበረ ያለው።