በክልሉ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት ሚና ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት ሚና ሊጠናከር ይገባል

ጋምቤላ፤ ሰኔ 7/2017 (ኢዜአ)፡-በጋምቤላ ክልል የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ መሠረት ማቲዎስ አመለከቱ።
ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ምክር ቤቶች ዓመታዊ የጋራ የምክክር መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል ።
በምክክር መድረኩ ላይ አፈ ጉባኤዋ እንዳሉት የተዋረድ ምክር ቤቶቹ የወከሉትን ህዝብ በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች በቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች የሚያዘጋጇቸው የልማት ዕቅዶች በአግባቡ መተግበራቸውን በመከታተልና በመቆጣጠር የህዝቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በተለይም የመንግስትን ውስን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ከድህነት ፈጥኖ ለመውጣት ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ከምክር ቤት አባላት የላቀ ሚና ይጠበቃል ብለዋል።
ህዝብ ለሚያነሳቸው የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ከመስጠት አንፃር ምክር ቤቶች ከአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ጋር ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በህገ መንግስቱ የተደነገጉ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩና በውጤቱም ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም አፈ-ጉባኤዋ ገልፀዋል።
'የዛሬው የተዋረድ ምክር ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክም ልምዶችን በመለዋወጥ የመደጋገፍ ባህላችንን ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል።
የምክክር መድረኩ አዘጋጅ የጋምቤላ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ኩዊች ዊው በበኩላቸው መድረኩ የተዋረድ ምክር ቤቶቹ የውክልና ተግባራቸውን በመፈፀም ረገድ ያሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት በቀጣይ ውስንነቶችን ለማረም እገዛ እንዳለውም ተናግረዋል።
በዚህም የጋምቤላ ከተማ ምክር ቤት በህገ መንግሥቱ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በአግባቡ ለመወጣት ከክልሉ ምክር ቤትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የተዋረድ ምክር ቤቶች የምክክር መድረክ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።