የትራፊክ አደጋን በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ - አገልግሎቱ

ድሬደዋ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፡- የትራፊክ አደጋን በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል የተጀመሩ አበረታች ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፌደራል የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አባሦ ተናገሩ። 

የፌዴራልና የክልሎች የዘርፉ አመራሮች በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍሎች የትራፊክ አደጋን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን በመመልከት የዘርፉን አፈጻጸም በድሬዳዋ እየገመገሙ ነው።


 

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉት የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አባሦ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የትራፊክ አደጋ በሰውና በሀገር ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።

ችግሩን በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል የ10 ዓመታት የተናበበ ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰው፤  ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጁ ስራዎች ለውጥ ማምጣት መቻሉን አውስተዋል።

ይህንን ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ አዳዲስ ዲጂታል ሪፎርሞች፣ ዘመናዊ አሰራሮችና ህጎች በመተግበር ላይ መሆናቸውን  ገልጸዋል።

በተለይ በምስራቅ ተጎራባች ክልሎች እየተገነቡ የሚገኙት የኮሪደር ልማቶች የትራፊክ ፍሰትን አስተማማኝ በማድረግ አደጋን ለማስቀረት ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አንሰተዋል።

እንደ ሀገር የተጀመረውን ዲጂታል የትራፊክ አደጋ የመከላከል ስራ በትክክል ዕውን በተደረገበት ድሬዳዋ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰው ተሞክሮውን በማስፋት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሹክሪ አብዱረህማን በበኩላቸው፤  ባለስልጣኑ ከፍትህ እና ከትራፊክ ተቋማት ጋር  ቅንጅት በመፍጠር አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በተለይ ከትምህርት ቤቶችና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር የተቀናጀ የትራፊክ አደጋ የመከላከል ስራ በመሰራቱ አደጋው እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

በምስራቅ ተጎራባች ክልሎች የተካሄደው የስራ ጉብኝት ለቀጣይ ስራ ጥሩ መደላድል እንደሚፈጥር በመግለጽ። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም