መገናኛ ብዙሃን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር መስራት ይገባቸዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር መስራት እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና እሁድ ኤ.አይ ስቱዲዮ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አሰራር ጥበብ ያሰለጠኗቸውን 25 የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስመርቀዋል።


 

ሰልጣኞቹ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የተውጣጡ ናቸው።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎቹ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በይዘት ስራዎች ላይ እሴት መጨመር የሚያስችል የጽንሰ ሃሳብና የተግባር ተኮር ስልጠና የወሰዱ ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ስልጠናው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚወስድ ነው።

በመሆኑም ሰልጣኞች የተማሩትን ወደ ተግባር በመለወጥ ሀገርን ለመቀየር የመስራት ሃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር፣ የወል ትርክትን ለመፍጠርና ሀገርን ለማበልጸግ የተያዙ ዋና ዋና እቅዶችን ለማሳካት ቴክኖሊጂውን ጥቅም ላይ በመዋል መስራት ይገባል ብለዋል።

በተመሳሳይ በተማሩበት ሙያ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ፊልሞችን በማምረት፣ ሌሎች ሙያተኞችን በማሰልጠን፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ጽንሰ ሃሳብን ግንዛቤ በመፍጠር መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ በመረዳትና በመገናኛ ብዙሃን የይዘት ስራዎች ውስጥ በመጠቀም ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ማጠናከርና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ማዋል እንደሚገባ በአጽኖኦት አንስተዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎችም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ እውቀት እንዲስፋፋ መስራት እንዳለባቸው በማስገንዘብ ተቋማትን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የማዘመን ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ በበኩላቸው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአግባቡ መጠቀም በድህረ እውነት በሀገር ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ይረዳል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተሰራ ለሚገኘው የአሰባሳቢ ትርክት ግንባታም አጋዥ መሆኑን ጠቅሰው፤ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የፈጠራ ስራዎችን ለመደገፍ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።


 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ኢ/ር ዶ/ር) በበኩላቸው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንደ ሀገር ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ጋር ለመሄድ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ጠቁመው፤ መገናኛ ብዙሃንም ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።


 

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የወሰዱት ስልጠና ለይዘትና ሌሎች ስራዎች ትልቅ አቅም በመፍጠር የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ ፋይዳው ትልቅ መሆኑንም የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎች ተናግረዋል።


 

በመሆኑም በተቋሞቻቸው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎችን ለመስራት ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩ አረጋግጠዋል።

ሰልጣኞቹ በበኩላቸው በስልጠናው ያገኙትን እውቀት የሀገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚያውሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም