ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ኮንፍረንሶች መልካም ገጽታን ከማስተዋወቅ ባሻገር የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚያግዙ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ኮንፍረንሶች መልካም ገጽታን ከማስተዋወቅ ባሻገር የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚያግዙ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኮንፍረንሶች የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ከማስተዋወቅ ባሻገር የዲፕሎማሲ ግንኙነትን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያግዙ ተገለጸ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ኮንፍረንሶች በስፋት እየተካሄዱ ይገኛሉ።
የአዲስ አበባ ከተማን የዲፕሎማቲክ መቀመጫነትና የአፍሪካ መዲናነት የሚመጥኑ መሰረተ ልማቶች መሟላት ደግሞ ለኮንፍረንስ ቱሪዝም መበራከት ምቹ ሁኔታን የፈጠሩ ናቸው።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የተለያዩ ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መደረጉም ሌላው እድል ነው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችም ይህንኑ ነው የሚያረጋግጡት።
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ አማረ ቀናው(ዶ/ር)፤ ከተማዋ የምታስተናግዳቸው ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ስብሰባዎች ከሀገር በጎ ገጽታ ግንባታ ያለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው።
የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የዲፕሎማሲ ስራ ለሀገር ወስጥም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማድረስ እንደሚያግዙ ተናግረዋል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን መሪ ስራ አስፈጻሚ አለማየሁ ጌታቸው፤ ኢትዮጵያ እየገነባቻቸው ያሉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችና የቱሪዝም መስህቦቿ ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ተመራጭ እንዳደረጓት ይገልጻሉ።
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና የሌሎች መሰረተ ልማቶች መሟላት አዲስ አበባን ለኮንፍረንስ ቱሪዝም የበለጠ ምቹና ተመራጭ እንድትሆን ማስቻላቸውን ተናግረዋል።
ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ የውጭ ዜጎች ስለኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎችና ባህላዊ እሴቶች በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ በሚካሄዱ ኮንፍረንሶች ገለጻ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ከተካሄዱ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ኮንፍረንሶች አራቱ በኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የጉባዔው ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ተሳትፎ የበለጠ ለማሳደግ ኮንፍረንሶቹ ዕድል የፈጠሩ ናቸው ብለዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላት ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፋ፤ ተቋሙ በቅርቡ ዓለም አቀፉን የአይዲ ፎር አፍሪካ ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱን አስታውሰዋል።
የተለያዩ ኮንፍረንሶችን ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝሙ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውንና በቱሪዝም ዘርፍ የተሻለ አቅም መፈጠሩንም ተናግረዋል።
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ አማረ ቀናው(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ኮንፍረንሶቹ ላይ የሚነሱ ሀሳቦች ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ የኮንፍረንሶቹን ጭብጦች በህትመት መልክ እንዲሰራጩ የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል።