ቋሚ ኤግዚቢሽኑ ከዓለም ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር የሚያወዳድር ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው ቋሚ ኤግዚቢሽን ኢትዮጵያን ከዓለም ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር የሚያወዳድርና የትውልዱን መጻዒ ዕድል በፈጠራና ምርምር የሚያግዝ መሆኑን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽንን በይፋ ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገን መስራት፣ ማየት እና መለማመድ የሚፈልጉ ሰዎች በሙሉ የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽንን እየመጡ መመልከት አለባቸው ብለዋል። 

ኢትዮጵያውያን ነገን መስራት ነገን መለወጥ ከፈለጉ ልጆቻቸውን ወደ ኤግዚቢሽኑ ሊያመጧቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።

ልጆቻችንም ይህ ትልቅ ዕድል እንደሆነ ተገንዝበው ክረምቱን ይህንን ቋሚ ኤግዚቢሽን በማየት ብዙ ትምህርት መቅሰም አለባቸው ሲሉም ገልጸዋል። 

ኤግዚቢሽኑ በውስጡ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የአካባቢ፣ የግብርና፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የስፔስና አቪየሽን ማሳያ ክፍሎችን አካቷል።

በዕለቱ ቋሚ ኤግዚቢሽኑን የቱሪዝም፣ የኪነ ጥበብ፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ጎብኝተውታል።

አስተያየታቸውን የሰጡ ጎብኚዎችም ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ባከናወነቻቸው ሥራዎች መደመማቸውን ነው ያነሱት።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ምን ያህል ውጤታማ ሊያደርግ እንደሚችል ያየንበት ነው ብለዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች አጋዥ በመሆኑ ትውልዱ ሳይንስን በአግባቡ በመረዳት ለአዳዲስ ፈጠራዎች እንዲተጋ የሚያግዝ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

የፍሎውረስ ኢቨንትስ ስራ አስኪያጅ ዮአዳን ጥላሁን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የቋሚ ኤግዚቢሽኑ መከፈት ተማሪዎች ሳይንስ ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ ፊልምና ትርኢት የማየት ዕድል እንዲያገኙና ከቴክኖሎጂ ጋር በደንብ እንዲተዋወቁ ያስችላል።

በቋሚ ኤግዚቢሽኑ ኢትዮጵያን በዓለም ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አይቻለሁ የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት መምህር ማስተር ምህረት ከድር ናቸው።


 

ጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ በበኩሏ፤ በሳይንስ ሙዚየም በቴክኖሎጂ የታገዘ የፈጠራ ትርኢትና ፊልም በአድናቆት መመልከቷን ገልጻለች።

ቋሚ ኤግዚቢሽኑ ትልቋ ኢትዮጵያን ከማሳየት ባለፈ የተፈጥሮ ጸጋ፣ የእድገትና የቴክኖሎጂ ልህቀት መሻቷን የሚያሳይ እንዲሁም ለተማሪዎች የነገ ተስፋ ለተመራማሪዎች ደግሞ ምቹና ሁሉን ያቀፈ ማዕከል መሆኑን ነው ያብራራችው።


 

ጋዜጠኛ ዮናስ ከበደ በሙዚየሙ የትናንት፣ የዛሬና የነገ ማንነታችንን ያየንበት ነው ብሏል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የደረሰችበት ከፍታ ትናንትን ያልረሳና ትውልድን ያስተሳሰረ መሆኑ ሁሉንም የሚያኮራ መሆኑን በማንሳት።


 

ጋዜጠኛ ዳዊት አበበም የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰው ልጆችን ህይወት በማቅለል በኩል የደረሰበትን ደረጃ በቀላሉ ማየትና በዚያ መጠቀም የሚያስችሉ ዕድሎች መፈጠራቸውን አድንቋል።


 

የሳይንስ ሙዚየምን በሰለጠኑ ሀገራት የመመልከት ዕድል እንደነበረውና በአጭር ጊዜ በኢትዮጵያ እውን ሆኖ ማየቱ አግራሞት እንደፈጠረበት የገለጸው ደግሞ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ ነው።

በሙዚየሙ ያገኘውን ዕድል ተጠቅሞ ለሀገርና ህዝብ ጠቃሚ የሆነ ፊልም ለመስራት ፍላጎት አንዳደረበት ጠቅሷል።


 

በቋሚ ኤግዚቢሽኑ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የህዋ ቅርጽ ሉላዊ የትዕይንት አዳራሽ ይፋ የተደረገ ሲሆን ስለ-ህዋ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው እጅግ አስደማሚ ምስሎችን በማቅረብ የህዋውን አለም እጅግ አቅርቦ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም