ማህበሩ ለእናቶች ማቆያ አገልግሎት የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ባህርዳር፤ ሰኔ 7/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደርና ሰሜን ጎጃም ዞኖች ለሚገኙ ሁለት ጤና ጣቢያዎች ለእናቶች ማቆያ አገልግሎት የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቃዱ ማዘንጊያ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ማህበሩ ግምታቸው 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፉን ያስረከበው ለክልሉ ጤና ቢሮ ነው።


 

ድጋፉም በደቡብ ጎንደር ጋህሳይና በሰሜን ጎጃም ሳንክራ ጤና ጣቢያዎች ለተገነቡ የእናቶች ማቆያ ማዕከላት መሆኑንም ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

ድጋፍ ከተደረጉት ቁሳቁስም አልጋዎች፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ የማብሰያ፣ የመመገቢያ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች፣ ቴሌቪዥን፣ ብርድ ልብስ፣ ለምግብ አገልግሎት የሚውል ዱቄትና ሌሎችም ይገኙበታል።


 

ቀደም ሲልም ማህበሩ የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ በክልሉ በዋግህምራ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ሰሜን ሸዋ ዞኖች ለሚገኙ አምስት ጤና ተቋማት ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ በአፋር፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በሲዳማ ክልሎች ማህበሩ መሰል ድጋፎችን በማድረግ የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ ሙያዊ ግዴታውን እየተወጣ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።


 

የክልሉ ጤና ቢሮ ተወካይ ዶክተር ቤተልሄም መኮንን እንዳሉት ማህበሩ በሁለት ጤና ጣቢያዎች ለተገነቡ የእናቶች ማቆያ ማዕከላት ያደረገው ድጋፍ የነበረውን የቁሳቁስ ችግር ሙሉ በሙሉ የቀረፈ ነው ብለዋል።

ይህም ራቅ ካሉ አካባቢዎች የሚመጡ ነፍሰ-ጡር እናቶች በማቆያ ማዕከላቱ ሳይቸገሩ ተገቢውን አገልግሎትና የባለሙያ ክትትልና ድጋፍ አግኝተው እንዲወልዱ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበሩ የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ እያደረገ ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ  እንዲውል ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

''ለጋህሳይ ጤና ጣቢያ የእናቶች ማቆያ የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ የነበረውን ችግር ሙሉ በሙሉ የቀረፈ ነው'' ያሉት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ ኃይለኢየሱስ ዳኘው ናቸው።

በክልሉ ከተገነቡ 727 የእናቶች ማቆያ ማዕከላት 544ቱ በአሁኑ ወቅት የተሟላ አገልግሎት ለነፍሰ-ጡር እናቶች እየሰጡ እንደሚገኙም ከክልሉ ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም