በምስራቅ ቦረና ዞን ከ115 ሺህ ለሚበልጡ የቀንድ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች የበሽታ መከላከያ ክትባት ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን ከ115 ሺህ ለሚበልጡ የቀንድ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች የበሽታ መከላከያ ክትባት ተሰጠ

ነገሌ ቦረና፣ ሰኔ 7/2017 (ኢዜአ) - በምስራቅ ቦረና ዞን ከ115 ሺህ ለሚበልጡ የቀንድ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች የበሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠቱን የዞኑ አርብቶ አደር ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የእንስሳት ጤና ባለሙያ አቶ ቦነያ አሬሮ ለኢዜአ እንደገለጹት እንስሳቱን ከሳንባ ምች፣ ከአባ ሰንጋ፣ ከአባ ጎርባ፣ ከቆዳና ከሌሎችም በሽታዎች ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ተሰጥቷል።
ክትባቱ ቆላማ በሆኑ ሊበን፣ ጎሮዶላ፣ አሬሮ፣ ዋጭሌ፣ ዳስና ጉሚ ኤልዳሎ ወረዳዎች እንደውም ወይናደጋማ በሆኑ መዳ ወላቡና ወላቡ ሊጣ ወረዳዎች መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
በወረዳዎቹ 400 ሺህ ለሚሆኑ የቀንድ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች ለመስጠት ታቅዶ እሰካሁን ለ115 ሺህ 480ዎቹ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በታቀደው መሰረት ክትባቱን ለማዳረስ በ600 የእንስሳት ጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች በመታገዝ እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል ።