በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 2 ሺህ 500 ቤቶችን በ90 ቀናት መልሶ ለመገንባት አቅደናል--ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በከፍተኛ ትኩረት 2 ሺህ 500 ቤቶችን በ90 ቀናት መልሶ ለመገንባት መታቀዱን  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መክፈቻ መርኃ-ግብር ተካሂዷል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 የቤት ማደስ ስራን አስጀምረዋል።

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል ሆኖ መቀጠል ያለበት መልካም ተግባር ነው።

በዚህም የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት የአንድ ወቅት የንቅናቄ ስራ ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ተግባር እና ባህል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተማዋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ባለሃብቶችን በማስተባበር የበጎ ሥራ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን  ገልጸዋል። 

በ2017 የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 18 ሰው ተኮር የሆኑ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ለመተግበር መታቀዱን አብራርተዋል።

በመርኃ ግብሩ ከተማዋን ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ እንድትሆን የሚያስችሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ከንቲባዋ አስታውቀዋል ።


 

በተጨማሪም ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች በድግግሞሽ ማዕድ የማጋራት ፣ወላጅ የሌላቸዉ ህፃናት አሳዳጊና ተንከባካቢ ቤተሰቦች የሚያገኙበት፣በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ከተማችንን አረንጓዴ የምናለብስበት ነው ብለዋል።

ከሁሉ በላይ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በከፍተኛ ትኩረት 2 ሺህ 500 ቤቶችን በ90 ቀናት መልሶ ለመገንባት መታቀዱንም ነው የገለጹት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ይመር ከበደ የክረምት ወቅት ለበጎ ፍቃድ ስራ ምቹ እና ተስማሚ ወቅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራበት እንደሚገኝ ጠቁመው ለስራው የሚያግዙ ቋሚ በጎ ፍቃደኞችን በማሰልጠን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ስራ ማስገባቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም