ህገ-ወጥ የምግብና የመድሃኒት ዝውውርን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር አለበት - ባለስልጣኑ

ሀዋሳ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ ህገ-ወጥ የምግብና መድሃኒት ዝውውርን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ከምግብና የጤና ግብዓቶች ቁጥጥር ባለድርሻ አካላት ጋር በሀዋሳ ከተማ ምክክር አድርጓል። 


 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በወቅቱ እንደገለጹት ባለስልጣኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት የምግብና መድኃኒት ቁጥጥሩን የሚያጠናክሩ የሪፎርም ስራዎችን በመተግበር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል። 

በዚህም የተመዘገቡ በርካታ ውጤቶች ቢኖሩም ያልተፈቱ ችግሮች በመኖራቸው ህገ-ወጥ የምግብና መድኃኒት ዝውውርን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር አለበት ብለዋል። 

ህገ-ወጥ የምግብና የመድኃኒት ዝውውር በሀገሪቱ እየጨመረ ለመጣው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መስፋፋት ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል። 

ዳይሬክተሯ አክለውም በምግብ ላይ ባዕድ ነገር መደባለቅ፣ ጥራትና ደህንነታቸው ያልተረጋገጡ መድኃኒቶችን በህገወጥ መንገድ በመሸጥ ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ለህግ የማቅረብ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዚህም ባለፉት 11 ወራት 243 የምግብ፣ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች አስመጪና አከፋፋዮች መታገዳቸውንና የ129ኙ ፈቃድ መሰረዙን ገልጸዋል። 

በተጨማሪም ለበርካታ ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንና የታሸጉ መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። 


 

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው በባለስልጣኑ የሚከናወኑ ተግባራት የማህበረሰቡን ጤንነትና ደህንነት ለማስጠበቅ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ናቸው። 

በክልሉ በዕቅድና በድንገተኛ ፍተሻ በህገወጥ የምግብና የመድኃኒት ዝውውር መከላከል ላይ በቅንጅት የተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የተመዘገቡባቸውና መጠናከር ያለባቸው ናቸው ብለዋል። 

በመሆኑም ባለድርሻ አካላት በመድረኩ የሚገኙ ግብዓቶችን የቀጣይ ዕቅድ አካል በማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የህዝቡን ጤና ማስጠበቅ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል። 

በክልሉ ህብተሰቡን ባለቤት ያደረገ የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ጤናና ጤና ነክ ግብዓት ጥራት ቁጥጥር አገልግሎት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ቡሪሶ ቡላሻ ናቸው። 


 

በዚህም ባለፈው አንድ ዓመት ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀልና ህገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውር ላይ ተሳትፈው በተገኙ 16 ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል። 

በቀጣይም የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት በማጠናከር ጉዳዩ በጤና ላይ እያስከተለ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት። 

በመድረኩ በባለስልጣኑና በሲዳማ ክልል ያለፉት ወራት አፈጻጸሞች ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም